ቀጥታ፡

የአፍሪካ–ቻይና የንግድ ትርዒት በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን አጋርነት ለማጠናከር ያስችላል ተባለ

አዲስ አበባ  ህዳር 18/2011 በአዲስ አበባ የሚካሄደው አፍሪካ – ቻይና የንግድና የኢንቨስትመንት ትርዒት በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን አጋርነት ለማጠናከር የጎላ ሚና አለው ተባለ። የአፍሪካ–ቻይና የንግድና የኢንቨስትመንት ትርዒት በመጪው ሳምንት ህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት በአዲስ አበባ የኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና የቻይና ዓለም አቀፍ ኤግዚቪሽን ማዕከል ተወካዮች ትርኢቱን አስመልክተው ዛሬ  መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫው ላይ እንደተመለከተው ትርዒቱ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል በፍጥነት እያደገና እየተስፋፋ የመጣውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገርን ኢላማ ያደረገ ነው። ከዚህም ባሻገር ትርዒቱ የአፍሪካና ቻይና ትብብር መድረክ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ በትርኢቱ ላይ በግብርና እና ምግብ ማቀነባበር፣  በቴክኖሎጂ፣ በሆቴል ዘርፍ፣ በማዕድን፣ በመኪና ማምረትና  በሌሎች ተዛማጅ  ዘርፎች የተሰማሩ 41  የቻይና ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የንግድ ሥራ ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያስችልና የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ መድረኮችም የትርኢቱ አካል ናቸው። በእነዚህ መድረኮች ላይ በኢትዮጵያ ስላሉ የቢዝነስ እድሎች ሰፊ ማብራሪያ ይሰጣል፤ የኢትዮጵያና የቻይና ኩባንያዎች በጋራ ሊሰሩባቸው በሚችሉት የኢንቨስትመንት መስኮች ላይም ትስስር ይፈጠራል ተብሎም ይጠበቃል። በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጉብኝትም ከትርዒቱ ጎን የሚካሄድ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል። ትርኢቱ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣  በቻይና የዓለምቀፍ ንግድ ማስፋፋያ ምክር ቤት፣ በቻይና አለም አቀፍ ኤግዚቪሽን ማዕከል እና በቻይና አፍሪካ የልማት ፈንድ ትብብር ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም