ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የቡና ልማትና ግብይት ለማሳደግ የሚያግዝ ዓለም አቀፍ የቡና ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ህዳር 18/2011 የኢትዮጵያን የቡና ልማትና ግብይት ማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ላይ የሚመክር ዓለም አቀፍ የቡና ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ከዘርፉ ጋር ተያያዥ የሆኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስብሰባ ማእከል ከህዳር 25 ቀን 2011 ጀምሮ ለሁለት ቀናት ነው የሚካሄደው። በጉባኤ ላይ በዓለም ደረጃ የሚታወቁ ቡና ላኪዎችን፣ አልሚዎችን፣ የቡና ገዢዎችን፣ የቡና ልማት ተመራማሪዎችን፣ የቡና ቆይና አቀናባሪዎችን እንደዚሁም የገበያ አስተዋዋቂዎችን ጨምሮ ከዘርፉ ጋር የተያያዘ ዓላማ ያላቸው ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ድርጅቶች ይሳተፋሉ ተብሎ  ይጠበቃል። ጉባኤው ለዘርፉ ልማትና አድገት የሚጠቅም ዓለም አቀፍ ልምድ የሚቀሰምበት መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ መሐመድ ሸምሱ ለኢዜአ እንደገለፁት ከጉባኤው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ቡና ግብይት በዓለም አቀፍ ገበያ የሚስፋፋበትን መንገድ መቀየስ ነው። ይህንንም እውን ማድረግ ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያን የቡና ልዩ ገፅታዎችን ለማስተዋወቅ፣ እሴት የታከለበት የቡና ልማትን ለማሳደግ፣ የቡና ልማትን በጥራትና በብዛት ማምረት በሚቻልበት መንገድ ከተለያዩ የዓለም አገራት የተጋበዙ ባለሙያዎች ጥናታዊ ፅሁፍ እንደሚያቀርቡ አቶ መሓመድ ገልፀዋል። በቡና  የአርሻ ልማት፣ ማዘጋጀት፣ ማቀናበርና ግብይት ሂደቶች ውስጥ የሴቶች ሚናና ተጠቃሚነት የሚጠናከርበትን  ስልት መቀየስም የጉባኤው ዓላማ ነው ተብሏል። ጉባኤውን በመተባበር የሚያዘጋጁት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የንግድ ሚኒስትር ናቸው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም