የዓመቱ የመጀመሪያ ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር በድሬዳዋ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓመቱ የመጀመሪያ ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር በድሬዳዋ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ህዳር 18/2011 የተያዘው ዓመት የመጀመሪያ ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር ህዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ይጀመራል። በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከ10 ክለቦች የተወጣጡ 70 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ማራቶን፣ ድሬዳዋ ከነማና ጎንደር ከነማ በውድድሩ ከሚሳተፉ ክለቦች መካከል ናቸው። ውድድሩ በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም፤ በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ክብደቶች ነው የሚካሄደው። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ተተኪ ቦክሰኞችን መመልመልና ብቁ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት የውድድሩ ዓላማ ነው። ይህ ውደድር በዓመቱ መጨረሻ በሞሮኮ ለሚካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን በቦክስ ውድድር ወክለው የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ያግዛል ተብሏል። ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በዓመት ለአራት ጊዜ የሚካሄድ መሆኑንና ቀሪዎቹ ውድድሮች በወላይታ፣ በጅግጅጋና በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። በአራቱም ብሔራዊ የቦክስ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ቡድኖች ውጤት ተደምሮ የ2011 ዓ.ም የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚሆኑም ነው አቶ ስንታየሁ ያስረዱት። ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድሩ እስከ ህዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል። በወንዶች ፌዴራል ፖሊስ በሴቶች አዲስ አበባ ፖሊስ የ2010 ዓ.ም የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል። በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የቦክስ ስፖርት እንደ አንድ የስልጠና ዓይነት በጦር ኃይል ውስጥ ለወታደሮች ይሰጥ ነበር። በተለይ በሐረር ጦር አካዳሚ የሚያሰለጥኑት እንግሊዞች በመሆናቸው የቦክስ ስፖርትን እንደ ዋነኛ የስልጠና ዓይነት ይሰጡ ነበር። በሰራዊቱ ውስጥ ከተቋቋሙ ክለቦች መካከልም የክቡር ዘበኛ፣ መኩሪያ፣ ምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሽ የሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ። ስፖርቱን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን በ1954 ዓ.ም ተመስርቷል።