ኢትዮጵያ ጾታዊ ትንኮሳን ለመከላከል በፖሊሲ እንድትደግፍ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ጾታዊ ትንኮሳን ለመከላከል በፖሊሲ እንድትደግፍ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ህዳር 17/2011 ኢትዮጵያ የጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳ ወንጀል መከላከል በፖሊሲ አለመደገፉ ወንጀሉን የመከላከል ሂደት አስቸጋሪ አድርጎታል ተባለ። ይህ የተባለው የጾታዊ ጥቃት ቀንን አስመልክቶ ሴታዊት የጾታ እኩልነት የተሰኘ ማህበር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ሴቶችና ከስዊዲን ኤምባሲ ጋር በመሆን በሰጠው መግለጫ ነው። ሴታዊት የጾታ እኩልነት ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሲሂን ተፈራ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የጾታ ጥቃት ፖሊሲ አለመኖር ወንጀሉን ለመከላከል ጫና ፈጥሯል። ጾታዊ ትንኮሳ በተለያዩ የአለም አገሮች የሚፈጸም ወንጀል ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ወንጀል መሆኑ በፖሊሲ አለመደገፉን አንስተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሴቶች ላይ የአሲድ ጥቃት ወንጀል እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ፍርድ እየተሰጠ ያለው በአካል መጉደል ብቻ መሆኑ በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም እነዚህና ሌሎች አዳዲስ በሴቶች ላይ እየተፈጸሙ ላሉ ወንጀሎች ከለላ ሊሰጥና ትክክለኛ ፍርድ ሊያስገኝ የሚችል የፖሊሲ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ሴታዊት የጾታ እኩልነት ማህበር የሴቶችን መብት በማቀንቀን የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲደረግ ግፊት ያደረገ መሆኑን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል። ስራ አስኪያጇ "ጉዳት የደረሰባትን ሴት የት ነበርሽ፤ ምን ለብሰሽ ነበር የሚሉ ጥያቄዎችን በማቅረብ ሴቷን ጥፋተኛ የማድረግ ልማዶች አሉ ሲሉ" በማለት የጥቃት ፈጻሚውን ጥፋት መሸፈንና በደሉን ሴቷ ላይ መጫን እንደሚንጸባረቅ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ጾታዊ ጥቃትን እንደ መብት የሚቆጥር ትውልድ መፈጠሩ ያሳስበኛል ሲሉ የድርጊቱን አሳሳቢነት ተናግረዋል። መገናኛ ብዙሃንን የሴቶችን ጥቃት ሪፖርት ሲያደርጉ "ምን አድርገሽው ነው፣ ምን ለብሰሽ ነበር" የሚሉ አገላለጾች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል። የተመድ ሴቶች የኢትዮጵያ ተወካይ ሜቲ ለቲ በበኩላቸው በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጾታዊ ጥቃት በሴቶች ላይ እያስከተለ ካለው ዘርፈ ብዙ ጥቃት ባለፈ በኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። የአለም ባንክ በቅርቡ በናይጀሪያ ያደረገው ጥናት በሴቶች ጥቃት ምክንያት አገሪቱ በአመት በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ማጣቷን ገልጸዋል። ኢትዮጵያም ጉዳዩ ምን ያህል ኪሳራ እያደረሰባት እንደሆነ መጠናት አለበት እንዳለበት መክረዋል። በኢትዮጵያ የስዊዲን አምባሳደር ቶርብጆን ቢተርሰን ጾታዊ ጥቃት ለአንድ አገር ብቻ የሚተው ጉዳይ ባለመሆኑ አለም በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል። በኢትዮጵያ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት በሚሰሩ ተግባራትን ደግፈው እንደሚሰሩም አምባሳደሩ ተናግረዋል። የጾታዊ ጥቃት ቀን በየአመቱ ከህዳር 16 እስከ ታህሳስ 1 ቀን ለ16 ቀናት ይከበራል።