ቀጥታ፡

የፖለቲካ ባህል ሽግግሩ የተሳካ እንዲሆን እንደፓርቲ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል-ተፎካካሪ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ  ህዳር 17/2011 የፖለቲካ ባህል ሽግግሩ የተሳካ እንዲሆን እንደፓርቲ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል ሲሉ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላት አስታወቁ። አመራር አባላቱ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ሽግግሩ አሁንም ሊሻገራቸው የሚገቡ በርካታ ፈተናዎች አሉት። ከነዚህም ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶች ዋናዎቹ ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም የዜጎችን የደህንነትና ተዘዋውሮ የመስራት መብት እያደናቀፈ እንደሆነ ገልጷል። በመሆኑም መንግስት የጀመረውን የፖለቲካ ለውጥ በሰከነ መንገድ ማካሄዱ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ በዜጎች ደህንነት ላይ ህግን በማስከበር ረገድ ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።ፖለቲካው በስርዓትና በህግ መመራት እንዳለበት ጠቁመዋል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ ገበረማሪያም በሰጡት አስተያየት "ዘላቂነት ያለው ፖለቲካል ሪፎርም በዚህ አገር አምጥቶ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስርአት የያዘ ፖለቲካ፣ በስርአት የሚመራ፣ ህግና ህግጋትን ብቻ የሚገዙት እንጂ የግለሰቦች ወደፈለጋቸው የሚጠመዝዙት አይነት ፖለቲካ እንዳይሆን ተቋማዊ መሆን አለበት" ብለዋል።  ማንኛውም ክልላዊ መንግስት ስርአት መጠበቅ አለበት ፤የዜጎች ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፣ ህዝብ ከህዝብ ጋር የሚያጋጩ ተግባራትን መቆጠብ አለብን፣ አሁን አጠቃላይ የህዝብ ደህንነት ጠብቆ በአንድነት የምንቀጥል ከሆነ ሁሉም ሰው እኩል እየታየ ሊገለገል ይገባል  ያሉት የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ናቸው፡፡  ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግስት የሚሰራቸው ስራዎች እንዳሉ ሆነው እንደፖለቲካ ፓርቲ ለውጡ እንዲሳካ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል። በመሆኑም መንግስት በሚያደርጋቸው እርምጃዎች ላይ ገንቢ ሃሳቦችን በማቅረብ፣ ጉድለታቸውን በመገምገምና አፈፃፀማቸው እንዲሳካ ለማድረግ የሚሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም በህዝብ መካከል ግጭት የሚፈጥሩ አስተሳሰቦችን በመቃዎምና ህዝብን በማረጋጋት ረገድም ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አረጋግጠዋል። አቶ ገብሩ እንዳሉት"የተሳሳቱትን እንዲታረሙ እየመከርን ሊታከሉ የሚገቡትን ገንቢ ሃሳቦችና አመለካከቶች በማፍለቅ አገራዊ መግባባት ብዙ ጊዜ የምንጮህለት፣ መግለጫ የምናወጣለት፣ የምንፅፍበት የምንነጋገርበት አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ ምን ጊዜም ወደኋላ አንልም እንቀጥልበታለን። በሰላማዊ መንገድ የምንታገል ተቃዋሚ ፓርቲ ነን ሃሳብ ነው ያለን ሃሳባችንን እናቀርባለን ለመንግስት አካላት የሚሰማ ካለ በተለያዩ መድረኮች አማራጭ ሃሳባችንን እናቀርባለን፣ ሰዎችም በኛ በኩል ወደ አመፅ እንዳይሄዱ ወደ ሌላ ነገር እንዳይሄዱ ማድረግ እንችላለን  ነው ያሉት አቶ አብርሃ ፡፡ የሶሻል ዴሞክራቲክ ህብረት ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው የሚደረገውን ሽግግር እንዲከናወን የምናደርገውን ምክርም፣ ወቀሳም ካለ ያንን እየሰጠን መቆየት ነው  ከመንግስት ጋር በሚኖረን ግንኙነት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም