የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ከእስር ተለቀቁ

71
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ክዌሲ ንያንታኪ በዋስ ተለቀቁ። የአገሪቱ ታዊቂ የምርመራ ጋዜጠኛ አናስ አርሜያው አናስ "ቁጥር 12" በሚል ርዕስ በጋና እግር ኳስ ውስጥ ስላለው ሙስና የሰራው ዘጋቢ ፊልም ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት መታሰር ምክንያት መሆኑ ይታወቃል። የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ዘጋቢ ፊልሙን ከተከታተሉ በኋላ የጋና የፖሊስ አገልግሎት የወንጀለኛ ምርምራ ክፍል የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥር ስር እንዲያውል በሰጡት ትዕዛዝ ክዌሲ ንያንታኪ ከትናንት በስቲያ ተይዘው ነበር። ተከሳሹ ትናንት ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን የጋና ፖሊስ የወንጀለኛ ምርምራ ክፍል በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ፍተሻ ማድረጉን አፍሪካን ኒውስ ዶት ኮም በድረ-ገጹ አስፍሯል። ክዌሲ ንያንታኪ ትናንት በዋስ የተፈቱ ሲሆን በተጠረጠሩበት ወንጀል የሚደረግባቸው ምርምራ እንደሚቀጥል ተገልጿል። የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክዌሲ ንያንታኪ ስልጣናቸውን በመጠቀም ያልተገባ ጥቅም ማግኘትና ሰዎችን በማታለል ገንዘብ ለመቀበል በሚል ክስ ይቀርብባቸዋል ተብሏል። በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 25 ዓመት የሚቆይ እስር እንደሚጠብቃቸው ተነግሯል። የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬኖች ማህበር ፊፋ እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ያሉት ነገር እንደሌለ የአፍሪካን ኒውስ ዶት ኮም ዘገባ ያመለክታል። የጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ክዌሲ ንያንታኪ በፖሊስ መያዛቸውንና ምርመራ መጀመሩ የጋና እግር ኳስ አፍቃሪን ያስደሰተና በአገሪቷ እግር ኳስ ላይ የሚታየውን ሙስና በግልጽ ያሳየ መሆኑን የስፖርቱ አፍቃሪው እየገለጸ መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም