ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሩዋንዳ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የባለብዙ መድረኮች የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማራመድ እንደሚሰሩ ገለፁ

አዲዲስ አበባ ህዳር 17/2011 ኢትዮጵያና ሩዋንዳ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የባለብዙ መድረኮች የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማራመድ እንደሚሰሩ ገለፁ፡፡ በሩዋንዳ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉስልጣን አምባሳደር ሉሊት ዘውዴ ከአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሪቻርድ ሲዝቤራ ጋር ሲወያዩ እንደገለፁት ከመደበኛ የሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ ስትራቴጂካዊ አጋር በመሆናቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር በመተባበር እየሰሩ ናቸው፡። በሁለቱ አገሮች መሃከል የተፈረሙ ስምምነቶች ትግበራ እየተካሄደ መሆኑንም አምባሳደር ሉሊት ተናግረዋል፡፡ አህጉራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን፣ በናይል ጉዳይ የተፈረመውን ስምምነት (Cooperative Framework Agreement) ያለፀደቁ አገራትን በማግባባት እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት የተቀመጡ የለውጥ ስራዎችን ተግባራዊ ከማድረግ እና አፍሪካ በዓለም ዓቀፍ ተቋማት ያላት ውክልና እንዲያድግ በጋር በመደጋገፍ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጠናክረው ለማስቀጠል በአገራችን በኩል ያለውን ቁርጠኝነትንም ገልፀዋል፡፡ ዶክተር ሪቻርድ በበኩላቸው ሩዋንዳ ከአገራችን ጋር ላላት ግንኙነት ከፍተኛ ትኩረት የምትሰጥ መሆኑን በመጠቆም በተለያዩ መስኮች የተጀመሩ ግንኙነቶችን በማጠናከር ትብብራቸውን ለማስፋት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ባለፈ ለአህጉሩም ማስፋት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡ በሁለትዮሽ ግንኙነት ረገድ በሂደት ላይ የሚገኙ የትብብር ስምምነቶችንም ከሶስተኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ አስቀድሞ ማጠናቀቅ አግባብ እንደሚሆን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መረጃ አመላክቷል። በተያያዘ ዜና በአፍሪካ የውሃ ሀብት ዘላቂ አጠቃቀም ላይ የሚያተኩር ዓለም አቀፍ ጉባኤ በኬንያ ናይሮቢ ተጀመረ። በጉባኤው የተሳተፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። የአህጉሪቱን የ'ሰማያዊ ኢኮኖሚ' ዘላቂነት ለመጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በሚመክረው በዚህ ስብሰባ ከ4 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። የስብሰባው ዓላማ የዓለማችን ውቅያኖሶች፣ ባህሮች፣ ሃይቆች እና ወንዞች ለሰብአዊ ፍጡር አገልግሎት መጠቀም በሚቻለበት መምከር ነው። ዓለም ባንክ በሚሰጠው ብያኔ 'ሰማያዊ ኢኮኖሚ' ማለት የውሃ አካላትን ጤናማ ሚዛን በማስጠበቅ ለኢኮኖሚ እድገትና ማዋልን መሰረት ያደረገ ተግባር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም