አፍላቶክሲን የወተት ጠንቅ ‼

14
ወንድማገኝ ሲሳይ (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብቷ በዓለም በመጀመሪያው ረድፍ ከሚቀመጡ አገራት አንዷ ናት ። ለልማቱም ተስማሚ የሆነ ብዝሃ ሕይወት፣የውሃ አካላት፣የአየር ፀባይና ስነ-ምህዳር አሏት። የተለያዩ ዓይነት የእንስሳት ዝርያዎችም በአርሶና አርብቶ አደሩ እጅ ይገኛሉ።የማዕከላዊ ስታቲስትክስ ኤጀንሲ በ2009 ዓ.ም ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው በሃገሪቱ 60.2 ሚሊዮን ዳልጋ ከብቶች በጉያዋ ይዛለች። ይህ ሰፊ ሃብት ታዲያ ለወተት ልማቱ አመቺ መሆኑ አያጠያይቅም።ይልቁኑም ለአርሶና አርብቶ አደሩ ኑሮ መሰረት በመሆን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል። ለዘርፉ እሴት ሰንሰለት ተዋናዮችም ገቢ በማሳደግ አገሪቱ ለጀመረችው ህዳሴ ጉዞ መሳካት የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው። ይሁን እንጂ እስካሁን  እንስሳት አርቢው የህብረተሰባችን ክፍል ከዚህ ልማት የላቀ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት። ከባለሙያዎቹ መካከል ዶክተር ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሐንስን በቅርቡ በወተት ጥራት አጠባበቅና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደበት ወቅት አነጋግረናቸው ነበር። እሳቸው እንደሚሉት አርሶና አርብቶ አደሩ በሀገሪቱ ካለው ሰፊ የእንስሳት ሀብት ወተትን በማልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ የእንስሳት እርባታ ስራው ከባህላዊ አረባብ ስርዓት ያልተላቀቀ መሆኑ ዋንኛው ነው። ገበያን መሰረት ያደረገ ምርት ለማምረት የሚያስችለው እውቀት፣ክህሎትና ግብዓት ተደራሽ አለመሆኑም እንዲሁ።የእንስሳት አያያዙም ቢሆን በልቅ ግጦሽ ላይ የተመሰረተ ከመሆኑም ባሻገር የገበያ መሰረተ ልማት አለመስፋፋቱም በምክንያትነት ይጠቅሳል። በተለይ በአገሪቱ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ የቆየው የወተት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ መወሰኑና ለምርት ጥራት የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ ነው ዶክተሩ የሚያስረዱት። በዚህም ምክንያት ተመርቶ ለገበያ እየቀረበ ባለው ምርት ላይ የጥራት ጉድለቶች በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ የተጠቃሚውን ህብረተሰብ ጤናና የአርሶ አደሩን ምርት ገበያ ቀጣይነት ለማረጋገጥ አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ ተገኝታል ባይ ናቸው። እንደሳቸው ገለፃ በአገሪቱ የተካሄዱ የምርምር ስራዎች እንዳረጋገጡት አርቢዎች በሚጠቀሙት የመኖ ግብዓት ጥራት መጓደል ምክንያት በወተት ምርት ላይ አፍላቶክሲን የተባለ መርዛማ ኬሚካል መጠን ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም በአፍላቶክሲን የተበከለ የወተት ምርት በተጠቃሚው ጤንነት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ ለመቀልበስ የሚያስችል ስራ መስራት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን በማሳሰብ። ሌላው የመድረኩ ተሳታፊና የወተት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ርህራሄ መስፍን እንደሚሉት አፍላቶክሲን የተባለ መርዛማ ኬሚካል በወተት ምርት ላይ የሚከሰተው የእንስሳት መኖን በጥራት ካለማምረት፣ ከአያያዝ  ጥንቃቄ ጉድለት የእንስሳት መኖው ለሙቀትና እርጥበት ሲጋለጥና የመኖ ንጥረ ነገሮች ሲበላሹ መሆኑን አስገንዝበዋል። ተመራማሪዋ እንደሚሉት በአፍላቶክሲን የተበከለ የወተት ምርት መጠቀም የጉበት ካንሰር ያስከትላል ። በማፍላትም ሆነ በፍሪጅ በማቀዝቀዝ መርዛማ ኬሚካሉን ማስወገድ አይቻልም ። ይህ ደግሞ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል ባይ ናቸው ። የእንስሳት መድሐኒት፣ መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንደሚገልጸው ደግሞ የወተት ጠንቅ የሆነውን አፍላቶክሲን ለመከላከል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ነው። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጠርዙ ዳያ እንዳሉት አፍላቶክስን በወተት ምርት ላይ የሚከሰተው በመኖ ደህንነት ጉድለት ነው። ይህንን መርዛማ ኬሚካል አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ባለስልጣኑ በየደረጃው በመኖ ደህንነት ላይ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ነው ያመለከቱት። ለንግድ አላማ በዋለው የመኖ ምርት ላይ ቁጥጥር በማድረግ ጥራት የሌለው ምርት እንዲወገድ እየተደረገ መሆኑን በመጠቆም። ከዘይት መጭመቂያ የሚወጣውን ተረፈ ምርት በመጠቀም መኖ በሚያቀነባብሩና በዘመናዊ የወተት ከብት እርባታ የተሰማሩ ድርጅቶች የሚጠቀሙትን ግብዓት ናሙና በመውስድ የላብራቶሪ ፍተሻ መጀመሩም እንዲሁ። ከተስማሚነት ምዘና ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በዚህ ዓመት በተደረገው ፍተሻ ከፋጉሎ፣ፍሩሽካና የበቆሎ ተረፈ ምርት ከሚዘጋጀው የመኖ ምርት ላይ ምንም ዓይነት ችግር አልተገኘም። የቅባት እህል ተረፈ ምርት በመጠቀም በተዘጋጀው የመኖ ምርት ላይ ግን ከፍ ያለ የአፍላቶክሲን ብክለት መገኘቱን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያስታወቁት። ይህ ችግር እየተፈጠረ ያለው በዋናነት በግንዛቤ ማነስና ከእርሻ ማሳ እስከ እንስሳት ቀለብ እስከሚውል ድረስ ባለው ሂደት በመሆኑ ለግንዛቤ ማስጨበጫ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ለችግሩም ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀራርበውና ተናበው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ በመግለጽ። የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የእንስሳት ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ተካ አፍላቶክሲን ውስብስብ ችግር ያመጣው ሳይሆን የእንስሳት መኖን በአግባቡ ከመያዝ፣ከማጓጓዝና ከማከማቸ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ችግር ነው ይላሉ። ይህ ችግር ከኢትዮዽያ አርሶ አደሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች አያልፍም የሚሉት ዳይሬክተሩ በጊዜ ካልተቆጣጠርነው ግን መዘዙ ከፍተኛ ነው ባይ ናቸው። በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ምልክቱ መታየቱን ጠቅሰው ችግሩን ከወዲሁ ለመቀልበስ የቁጥጥሩን ስራ በቅንጀት ለመስራት ጥረት መጀመሩን አውስተዋል። የንቅናቄ መድረክ እስከ ቀበሌ ድረስ ማቀጣጠል ወሳኝ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ታሪኩ ይህን ለማስፈጸም ሚኒስተሩ የወተት ጥራት ማስጠበቂያ የስልጠናና ምክረ ሃሳብ መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል። በሚኒስቴሩ የግብዓት ግብይትና አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ኢዮብ አለሙ በበኩላቸው በአገሪቱ በወተት ምርት ላይ ተከስቶ በነበረው አፍላቶክሲን ምክንያት በዘርፉ ላይ ችግር መድረሱን ይናገራሉ። ችግሩን መሰረት ባደረገ መልኩ የተለያዩ ጥናቶችና ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ያሉትን ግድፈቶች ለማረም በህግና በማእቀፍ በመደገፍ የተሻለ አሰራር ለመፍጠር እየተሰራ ነው። በዚህ ረገድ ረቂቅ ህጎች እየተቀረጹ ያሉበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸው ወተትን ለማምረት ደረጃውን የጠበቀ መኖ ማምረትና አያያዙን ማሻሻል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳይደለ በማሳሰብ። ካለፈው ዓመት ወዲህ የእንስሳት መኖ ጥራት የሚቆጣጠር የላብራቶሪ ማዕከል በማቋቋምና በሰው ሃይልና በማቴሪያል በማደራጀት ስራ ውስጥ ተገብቷል። በቀጣይ ጥራት ያለው የመኖ ኤክስቴንሽን በሁሉም ደረጃ ለማስፋፋት፣አርሶና አርብቶ አደሩን፣መኖ አቀነባባሪዎችን፣የወተት አምራች ኢንዱስትሪ አካላትን ለማብቃትም ጥረት ይደረጋል ይላሉ። የኢትዮዽያ ወተት ኢንዱስትሪ አቀነባባሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ በላቸው ሁሪሳ የአፍላቶክሲን ችግርን ለመከላከል የሻገተና የተበላሸ መኖ ለእንስሳት እርባታው እንዳይቀርብ ማድረግ ያስፈልጋል። በመኖ ማቀነባበሪያ የሚመረተውን የምርት ሂደቱን መከታተልና ጤናማ የሆነ የመኖ ምርት ብቻ ገበያ ላይ እንዲቀርብ የተጀመሩ ጥረቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል። በመሆኑም በወተት ምርት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ እንዲቻል የአረባብ ሥርዓቱን፣ አመጋገብና የጤና አያያዝን በማሻሻል ጥራቱን የጠበቀ የወተት ምርት ገበያ ላይ እንዲውል ማድረግ የሁሉም የዘርፉ ተዋናዮች የቤት ስራ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም