ጅማ አባ ጅፋር ነገ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከጅቡቲ ቴሌኮም ጋር ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ጅማ አባ ጅፋር ነገ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከጅቡቲ ቴሌኮም ጋር ያደርጋል
አዲስ አበባ ህዳር17/2011 ጅማ አባ ጅፋር የ2018/19 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ነገ ከጅቡቲ ቴሌኮም ጋር ያደርጋል። አህጉራዊው የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ነገ በጅቡቲ በሚደረጉ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ይጀመራል። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ በመሆን ኢትዮጵያን የሚወክለው ጅማ አባ ጅፋር 10 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታድ ዱ ቪል ስታዲየም ነገ ከምሽቱ 12 ሰዓት ከጅቡቲ ቴሌኮም ጋር ይጫወታል። በአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ የሚሰለጥነው ጅማ አባ ጅፋር በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ በሚያደርግበት የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ትናንት ማምሻውን 18 ተጫዋቾቹን ይዞ ወደ ጅቡቲ አቅንቷል። ክለቡ ጨዋታውን በሚያደርግበት በስታድ ዱ ቪል ስታዲየም ልምምዱን እያደረገ ይገኛል። በ1975 ዓ.ም የተመሰረተው ጅማ አባ ጅፋር ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደገበት 2010 ዓ.ም በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እየተመራ ሻምፒዮን በመሆን ስኬታማ የውድድር ዓመት ማሳለፍ መቻሉ ይታወቃል። ክለቡን ውጤታማ ያደረጉት ተጫዋቾች በመልቃቀቸው ምክንያት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑ እንደገና እየተደራጀ ይገኛል። ባለፈው የውድድር ዓመት በሊጉ 23 ግብ በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢ የነበረው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ጨምሮ ተመስገን ገብረኪዳን፣ ሄኖክ አዱኛና ዮናስ ገረመው ከለቀቁት ተጫዋቾች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ጅማ አባ ጅፋርን የተረከቡት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ባደረገው አንድ ጨዋታ አዳማ ከተማን 2 ለ 0 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል መጀመሩ ይታወሳል። እስከ አሁን በተደረጉ ጨዋታዎች ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ጅቡቲ ቴሌኮም ሰባት ጊዜ የጅቡቲ ፕሪሚየር ሊግን ያሸነፈ ሲሆን የጅቡቲ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ሁለት ጊዜ ማንሳት የቻለ ክለብ ነው። በዘንድሮው ዓመት የጅቡቲ ፕሪሚየር ሊግ ባደረገው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፎ በአንድ አሸንፎ በሦስት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጅማ አባ ጅፋር በደርሶ መልስ ጨዋታውን ካሸነፈ ከባለፈው ዓመት የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ ከነበረው የግብጹ አል አህሊ ጋር በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ይጫወታል። በሌላ በኩል የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ አሸናፊ በመሆን ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚወክለው መከላከያ ከናይጄሪያው ኢኑጉ ሬንጀርስ ጋር ከነገ በስቲያ ይጫወታል። በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚሰለጥነው መከላከያ በናምዲ አዚኪዌ ስታዲየም ለሚያደርገው ጨዋታ 18 ተጫዋቾችን ይዞ ነገ ወደ ናይጄሪያ ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል። የመልስ ጨዋታውንም ህዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርግ ሲሆን መከላከያ የደርሶ መልስ ጨዋታውን ካሸነፈ በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ከአልጄሪያው ዩኤስኤምቤል አቤስ ወይም ከላይቤሪያው ኤልአይኤስሲአር አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል።