አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የብዙሀን መገናኛ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

19
ሃዋሳ ግንቦት 16/2010 አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማጎልበት የብዙሀን መገናኛ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው የደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መክፈቱን አስመልክቶ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሃዋሳ ከተማ ተወያይቷል፡፡ የደቡብ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሉ እንደተናገሩት በክልሉ ለሚከናወኑ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ሥራዎች ስኬታማነት የብዙሀን መገናኛ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የአማራ ብዙሀን መገናኛ ከክልሉ ውጭ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከፍቶ ለመንቀሳቀስ መወሰኑ ለሕዝቡ አማራጭ የመረጃ ምንጭ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ አቶ ሰለሞን እንዳሉት አንድ የፓለቲካና የኢኮኖሚ ማህብረሰብ ለመገንባትና አገራዊ ራዕይ እንዲሳካ ብዙሀን መገናኛ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ "የክልል መገናኛ ብዙሀን በሌላ በተለያዩ ክልሎች ተንቀሳቅሰው መስራታቸው የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል" ያሉት አቶ ሰለሞን በደቡብ ክልል ያለውን ብዝሃነትና ሃብት በማስተዋወቅ በኩልም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ አለባቸው የሱፍ ተቋሙ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ የተለያዩ ብዙሀን መገናኛዎች ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "ሚዲያ ሃገር እንጂ ድንበር የለውም" ያሉት ሥራ አስኪያጁ ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃን ለሕብረተሰቡ ከመስጠት ባለፈ የህዝብን እሴቶችና የአገሪቱን ገጽታ ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል፡፡ የአማራ ብዙሃን መገናኛም የመረጃ ተደራሽነቱን በማስፋት ህዝቡ በስፋት የሚናገርበትና የሚያደምጥበት ለመሆን ከመስራት ባለፈ ህብተሰቡን በላቀ ደረጃ ለማገልገል መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ አለባቸው ገለጻ  በአገሪቱ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ጥረት ብዙሀን መገናኛ በተናጥል ሳይሆን በጋራና በተደራጀ አግባብ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዝን ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ሃብቴ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ ያሉ ሁሉም ብዙሀን መገናኛ ሕብረተሰቡን የማገልገል ተመሳሳይ ተልእኮ አላቸው፡፡ የአማራ ብዙሀን መገናኛ በደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከፍቶ በቅንጅት መስራቱ የሕብረተሰቡን መረጃ የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብት የሚያጎለብት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ብዙሃን መገናኛ በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ አሰራር መከተላቸው ሕብረተሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው የገለጹት አቶ ብሩክ፣ ተወዳዳሪነትና ጥራት ያለውን መረጃ ለማድረስ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ "ለሚዲያ ተቋማት ትልቁ ግብዓት መረጃ በመሆኑ መረጃ በስፋት የሚያገኙ የሚዲያ ተቋማት ተገቢውን መረጃ ለሕብረተሰቡ የማድረስ አቅም ይኖራቸዋል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በማንኛውም አጋጣሚ ለህዝብ የሚከለከሉ መረጃዎች ሊኖሩ እንደማይገባ የገለጹት አቶ ብሩክ የክልሉ ብዙሀን መገናኛ የመረጃ እጥረቱን ለመቅረፍ በተለያዩ ቋንቋዎች ስርጭት እያካሄደ መሆኑንና አስገንዝበዋል፡፡ በውይይት መደረኩ ላይ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከተለያዩ ተቋማትና አደረጃጀቶች እንዲሁም ከከተማ ነዋሪዎች የተወከሉ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆኑ የድርጅቱን የእስካሁኑን ሂደት የሚያሳይ ሰነድም ቀርቦ ውይይት ተደርጓበታል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም