ቀጥታ፡

የትራንስፖርት ዘርፍ ሕግና መመሪያዎችን ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር ለማስማማት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ  ህዳር17/3/2011 ኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፍ ሕግና መመሪያዎቿን ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር ለማስማማት እየሰራች መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ። የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ሕግ ከጎረቤት አገራትና ከሦስት የቀጣናው አገራት የምጣኔ ኃብት ማኅበረሰብ የዘርፉ ሕጎች ጋር ያነጻጸረ ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።   የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ)፣ የምስራቅ አፍሪካና የደቡብ አፍሪካ የልማት ማኅበረሰብ (ሳድክ) የሦስትዮሽ የትራንስፖርት መርኃ ግብር መስርተዋል። የአከባቢውን አገራት የትራንስፖርት ሕጎች፣ መመሪያዎችና ሌሎች የአሰራር ሥርዓቶች በማቀናጀት በቀጣናው የተሳለጠ የትራንስፖርት ሥርዓት ለመዘርጋት እየሰራም ይገኛል። ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በትራንስፖርት ዘርፍ ልታሻሽላቸው የሚገቧት በርካታ ሕጎችና የአሰራር ሥርዓቶች መኖራቸውን ነው የመርኃ ግብሩ ቡድን መሪ ጌሪት ፊሸር የሚገልጹት። እርሳቸው እንደሚሉት በመንጃ ፍቃድ አሰጣጥ በተለይም መታወቂያው ላይ በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ስለሚጻፍ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ደረጃ ጋር ማጣጣም አይቻልም። በዓለም አቀፍ ደረጃ መሰረት በመንጃ ፍቃድ ላይ መስፈር የሚገባቸው ጠቃሚ መረጃዎችም እንደሌሉና መንጃ ፍቃድን በየደረጃው በተለያዩ ቀለማት የማቅረብ ክፍተት መኖሩንም ጠቁመዋል። ታርጋዎችን የመሰየምና መለያ የመሰጠት ክፍተት መኖሩን የጠቆሙት ቡድን መሪው 'ኢቲ' የተሰኘው የእንግሊዝኛ ፊደል የታርጋ መለያም የኢትዮጵያ ሳይሆን የሌላ አገር እንደሆነ ነው የተናገሩት። የተመዘገበው 'ኢቲ' የእንግሊዝኛ መለያ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ሥምምነት መሰረት የግብጽ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን መለያውን እየተጠቀመችበት መሆኑን አስረድተዋል። የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ፍተሻን በተመለከተም የተለያዩ የተሽከርካሪ አካላትን ለይቶ በመፈተሽና ብቃታቸውን በማረጋገጥ ረገድ 'ክፍተት አለ' ብለዋል። የውጭ አገር ተሽከርካሪዎችን የተመለከተ ሕግ ጭምር አለመኖሩንም ነው ያስቀመጡት። የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በትራንስፖርት ዘርፉ ያሉ ሕጎችና የአሰራር ሥርዓቶች ላይ የማሻሻያ ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል። በተለይም አገሪቱ የባህር በር የሌላት በመሆኗ በትራንስፖርት ዘርፍ የምታወጣቸውን ሕጎች ከጎረቤት አገራት ሕጎች ጋር ለማጣጣም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። እየተካሄደ ያለው ማሻሻያ ፍትሃዊነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥና የዘርፉን ቴክኖሎጂዎች መጠቀም በሚያስችል መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ 90 በመቶ የሚሆነው እቃ የሚጓጓዘው በመንገድ ትራንስፖርት መሆኑን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም