ቀጥታ፡

በቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ጣና ባህርዳርና ሙገር ሲሚንቶ ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ ህዳር 17/2011 ትናንት በተካሄዱ የ2011 ዓ.ም የወንዶች ሐበሻ ሲሚንቶ የቮሊቮል ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር ጣና ባህርዳርና ሙገር ሲሚንቶ አሸንፈዋል። በሊጉ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል። በዚሁ መሰረት አራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በፈጀው የመጀመሪያው ጨዋታ ጣና ባህርዳር አዲስ አበባ ፖሊስን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በሁለተኛው ጨዋታ ሙገር ሲሚንቶ በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲን 3 ለ 2 ማሸነፍ ችሏል። ከትናንት በስቲያ ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ሲጀመር መከላከያ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 3 ለ 2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል። ትናንት ሶዶ ላይ ወላይታ ዲቻ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በእንግዳው ክለብ ጠያቂነት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ከ2005 ዓ.ም አንስቶ በሁለቱም ጾታዎች የፕሪሚየር ሊግ ውድድር እያካሄደ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም