ቀጥታ፡

ስሑል ሽሬና አዳማ ከነማ አቻ ተለያዩ

ሽሬ ህዳር 17/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ትናንት የተገናኙት ስሑል ሽሬና አዳማ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። በሊጉ የሦስተኛ ሳምንት ውድድር ሽሬ እንዳስላሴ የተገናኙት ክለቦች ግብ ሳያስቆጥሩ ባዶ ለባዶ ተለያይተዋል። እንግዳው ክለብ በመከላከል ላይ የተመሰረተ ጨዋታ በመምረጡ ወደ ግብ ክልል የቀረበባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። የአዳማ ከነማው 17 ቁጥሩ አክርሮ የመታትና አግዳሚ ከመለሰበት ሙከራ ውጭ በጨዋታው የረባ የግብ ሙከራ አልታየም። የስሑል ሽረ የእግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በሰጡት አስተያየት ተጫዋቾቻቸው ተረጋግተው ባለመጫወታቸው ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት መገደዳቸውን ተናግረዋል።ምክንያታቸው በሜዳቸው አሸንፈው ለመውጣት የነበራቸው ጉጉት ነበር። የአዳማ ከነማ የእግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃም በበኩላቸው ያጋጠሙንን የግብ ዕድሎች በአግባቡ ባለመጠቀማችን ነጥብ ተጋርተን ወጥተናል ብለዋል። የከተማው ነዋሪዎች ላደረጉላቸው አቀባበል ምስጋናና እግር ኳስ አፍቃሪዎች ላሳዩት ጨዋነት ለተሞላበት አደጋገፋቸውም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።በሌሎች ከተሞችም ይህንን መሰል የድጋፍ ሥርዓት መለመድ እንዳለበትም አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የዘንድሮውን ውድድር መቀሌ 70 እንደርታ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ሐዋሳ ከነማ ስድስት ነጥቦች በማስቆጠርና በግብ ልዩነቶች ተበላልጠው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው በመምራት ላይ ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም