ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ መቆራረጥና መጥፋት በሥራና በዕለት ተዕለት ኑሯችን ላይ ችግር እየፈጠረ ነው....በድሬዳዋ ነዋሪዎች

ድሬደዋ ህዳር 16/2011 የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መጥፋት በሥራና በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ላይ ላይ ችግር እየተፈጠረ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው በድሬዳዋ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች ጠየቁ። የነዋሪዎችን ቅሬታ የተቀበለው የድሬዳዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታው ፕሮጀክት እስከ መጋቢት ወር 2011 ድረስ ይጠናቀቃል ብሏል፡፡ ለአዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል በሳቢያን አካባቢ በእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ማህበራት በተደጋጋሚ ጊዜ መብራት መጥፋትና መቋረጡ በሥራቸው ላይ አሉታዊ ጫና እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡ ከራሳቸው ባለፈ 12 ወጣቶች ቀጥረው የሚያሰሩት አቶ ዘውዱ ተፈራ እንደተናገሩት ደንበኞቻቸው ያዘዙትን ሥራ በጊዜ ማድረስ ባለመቻላቸው አመኔታ እያሳጣቸው መሆኑን ተናግረዋል። በ"ቢንያም የእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ ድርጅት" ተቀጥሮ የሚሰራው ወጣት አህመድ ሐሰን በበኩሉ መብራት ለሶስት ቀናት የሚጠፋበት ወቅት መኖሩን ጠቁሞ ለነገ የተሻለ ሕይወት የሚቆጥበውን ገንዘብ ለመጠቀም እንዳስገደደው ገልጿል፡፡ "በመብራት መጥፋት ሳቢያ የስኳር ህመምተኛ ባለቤቴ መድኃኒት ተበላሽቶ ለችግር ተጋልጠን ነበር" ያሉት በድሬዳዋ የነምበርዋን ነዋሪ አቶ አየለ ተሰማ ናቸው፡፡ "የመብራት ኃይል ህዝቡን ለብሶት እየዳረገ ላለው የኃይል እጥረት ችግር መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል" ብለዋል፡፡ ከድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም ገንዘብ ተበድረው የፀጉር ሥራ መጀመራቸውን የተናገሩት የነምስራች ሀብታሙ ማህበር አባላት የመብራት መጥፋትና መቆራረጥ በሥራው ላይ ጫና በመፍጠሩ ብድራቸውን ለመክፈል እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡ የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ምስራች ደምሴ "እንኳን ሰርተን ልንለወጥ ይቅርና ያለብንን እዳ መክፈል አቅቶናል"  ብላለች፡፡ በኤሌክትሪክ መቆራረጥ  ምክንያት ፍሪጅና ቴሌቪዥናቸው መቃጠሉን የጠቆሙት የገንደቆሬ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ ከማል በበኩላቸው ያረጁ መስመሮች እየተበጣጠሱ በሰውና በንብረት ላይ አደጋ እየፈጠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ተመሳሳይ ሃሳብን ያላቸው ወይዘሮ መሰረት ከልክሌ በኤሌክትሪክ ሳቢያ ለአራት ጊዜ ያቦኩትን ሊጥ ለመድፋት መገደዳቸውንና ህዝቡን እያመረረ ላለው ችግር መንግስት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ሰለሞን አሰፋ የቬራ ፓስታ ፋብሪካ ሠራተኛ በመብራት መጥፋት ምክንያት በፋብሪካው ምርትና አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ኪሰራ እየደረሰ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሚያደርሰው ጉዳት ሊጠየቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የነዋሪዎቹን ቅሬታ ያመኑት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የድሬዳዋ ዲስትሪክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቅረማርያም አለማየሁ በበኩላቸው "አብዛኛዎቹ የኤሌክትሪክ መስመሮችና የኃይል ማሰራጫዎች ከ20 ዓመት በፊት የተገነቡና የተዘረጉ በመሆናቸው ለኃይል መቆራረጥ መንስኤ ሆነዋል" ብለዋል፡፡ አሁን እየተፈጠረ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ድሬዳዋን ጨምሮ በ8 የሀገሪቱ ከተሞች እየተኪያሄደ የሚገኘው የኮንክሪት መስመርና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክት በመጋቢት ወር ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት ሲጀምር ችግሩ 80 በመቶ እንደሚፈታ አስረድተዋል፡፡ የድሬዳዋ ፕሮጀክት 92 በመቶ እንደተጠናቀቀና ይህንን ፕሮጀክት ለማሳካት ሲባል መብራት እንደሚቋረጥም ጠቁመዋል፡፡ "ከዚህ ጎን ለጎን በ55 ሚሊዮን ብር በገጠርና በከተማ የተጀመረው 73 ኪሎ ሜትር ያረጁ መስመሮችን የማሻሻልና የማሳደግ ሥራ እስከ ሰኔ ወር በማጠናቀቅ ቀሪው 20 በመቶ  ችግር በመፍታት የነዋሪው ጥያቄ ይመለሳል" ብለዋል፡፡ ወደፊት መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መስሪያ ቤቱ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ መጠነኛ የዋጋ ማሻሻያ እንደሚያደርግም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም