ባንኩ ለማዕከሉ የ10 ሚሊዮን ብርና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ ለማዕከሉ የ10 ሚሊዮን ብርና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ህዳር 16/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመቄዶንያ የአረጋዊያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የ10 ሚሊዮን ብርና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። ድጋፉን የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ዛሬ ለማዕከሉ አስረክበዋል። የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ድጋፉ የባንኩ አመራሮችና ሰራተኞች ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት ለመስጠት ቃል ከገቡት መካከል ነው። ከ10 ሚሊዮን ብሩ በተጨማሪ 5 የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ 25 የልብስ መተኮሻ ካውያዎች፣ 8 የሥጋ መፍጫ ማሽኖች፣ 7 ቴሊቪዥኖች፣ 2 ላፕ ቶፕ ኮንፒውተሮችና 2 የውሃ ማጣሪያዎች መለገሱም ተገልጿል። ማዕከሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በአገሪቷ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የማዕከሉን ዓላማ በሃሳብና በገንዘብ መርዳት ሌሎችንም ሰዎች ለመሰል ዓላማ ለማነሳሳት ይረዳል ብለዋል። ባንኩ በየጊዜው የሚያደርገው ድጋፍ ስጦታ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነም ተናግረው በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በተለይም ማዕከሉ እያሰገነባ ላለው ባለ 10 ወለል ህንፃ በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።