ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡን ፈር ለማስያዝ መገናኛ ብዙሃን ከአጀንዳ ተቀባይነት መውጣት አለባቸው

ህዳር 15/ 2011 የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ መሰረት እንዲይዝ መገናኛ ብዙሃን ከአጀንዳ ተቀባይነት ወጥተው ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ እንደሚገባቸው የዘርፉ ምሁራንና አመራሮች ተናግረዋል። በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተሞከሩ ፖለቲካዊ ለውጦች በዴሞክራሲያዊነት ጉድለት ሳይሳኩ መቅረታቸው  የመገናኛ ብዙሃን ድርሻ የጎላ  እንደሆነ በተለያዩ ግዜያት ይነገራል። የአሃዱ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ  አቶ ጥበቡ በለጠ ሀገሪቱ ከጥቂት ጊዜያት በፊት የመበታተን ስጋት ሲደቀንባት ሁኔታዎችን በማረጋጋት ሚዲያዎች ምንም ዓይነት ሚና እንዳልነበራቸው ነው የሚናገሩት። የግሉ ሚዲያም በመንግሥት ጫና በመዳከሙ  ችግሮችና የግጭት ዜናዎች ሲዘገቡ የነበሩት በማህበራዊ የትስስር ገጾችና በውጭ መገናኛ ብዙሃን እንደነበረም ጠቁመዋል። የሀገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙሃንም ከአንድ ፓርቲ የሚመነጩ ዘገባዎች ላይ ማተኮራቸው መንግስት መሬት ላይ ያለውን እውነታ መመልከት እንዳይችል ማድረጉን ይገልጻሉ። “መንግስት ጋዜጦችንና መጽሄቶችን ማፈኑ ራሱን ነው የጎዳው፥ ሚዛናዊ ዘገባዎች በመቅረታቸው ክፍተትን በማመላከት፤ መፍትሔ ጠቋሚ ዘገባ ባለመኖሩ ቀውስ ላይ ወድቀን ነበር” ነው  ያሉት አቶ ጥበቡ። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ አየለ አዲስ እንደተናገረው ከ7 ወራት በፊት መገናኛ ብዙሃኑን የሚያስተባብሩ የመንግሥት ተቋማት ሚናቸው የተዳከመ በመሆኑ ሀገራዊ አንድነትን ከመገንባት ይልቅ ልዩነት አባባሽ ሆነው ቆይተዋል። ጦማሪ በፈቃዱ ሃይሉ በበኩሉ በኢትዮጵያ የነበረው የሚዲያ አፈና የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዲዳከሙ፤ የቀሩትም ሃላፊነት የጎደላቸው መረጃዎችን እንዲያሰራጩ ምክንያት ሆኗል ይላል። አሁን ያለውን ለውጥ መሰረት ለማስያዝ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለረጅም ዓመታት የተጓዙበትን አደረጃጀት በመቀየር የጋዜጠኞችንና የተቋማትን ሙያዊ አቅም ማሳደግ እንደሚገባም አቶ ጥበቡ  ገልጸዋል። በሚመሩት ሬዲዮም ጋዜጠኞች ሙያዊ ቁመና እንዲላበሱ በማድረግ በሚዛናዊነት ለመንግሥት አቅጣጫ የሚጠቁሙ መረጃዎችን እያቀረብን ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሄኖክ ስዩም እንዳሉት ከሰባት ወራት በፊት እንግልት የተፈጸመባቸው ጋዜጠኞችና ሚዲያዎች ለውጡን  ተከትሎ ወደ ሥራ  በመመለሳቸው የህዝብም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን ገለልተኛ ሆነው ለውጡ  ማገዝ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሀገሪቱ ህዝብ ልሳን ለመሆን እየተደራጀ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ ድክመቶቹን በማረም እውነተኛ ሚዲያ ለመሆን በትኩረት ይሰራልም ብለዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ አቤል አዳሙ በበኩላቸው የሚመሩት ሚዲያ ጉድለቶች ቢኖሩትም ሀገራዊ ለውጡን መሰረት ለማስያዝ እየሰራ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡ “መንግስትም አፈቀላጤ ሁኑኝ  ብሎ አያውቅም፣ እኛም መንግስት ውስጥ ሄደን የምንወሸቅበት ምንም ምክንያት የለም፣ ሆኖም ኢቢሲ አጀንዳ ቀረጻ ላይ የተዋጣለት ነው ማለት አይቻልም” ሲሉም ገልጸዋል። ጋዜጠኞች የራሳቸውን አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ላይ ሳይጭኑ፤ መረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል ያሉት አቶ አቤል በ”ዓይናችን” ዘገባዎች ላይ ተመስርቶ በርካታ አመራሮች እርምጃ እንደተወሰደባቸው ገልጸው ለምርመራ ዘገባ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ያለመሆን ችግሮች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ለውጥ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከእያንዳንዱ መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኛ የአስተሳሰብና ተቋማዊ ለውጥ መጀመር  አለበት ያለው ደግሞ ተማሪ አየለ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን የተሻለ የአሰራር ነጻነት ተፈጥሯል ያለው የሸገር ታይምስ መፅሄት ዋና አዘጋጅ ሰሎሞን ታደሰ፤ አንዳንድ ባለስልጣናት የግል ሚዲያውን መረጃ ለመከልከልና ለመደበቅ የያደርጉት ጥረት የመንግስትን ዓላማ የሚቃረን ነው ብለዋል። ሸገር ታይምስ መፅሄት ሀገራዊ ለውጡን በመደገፍ መስተካከል የሚገባቸው ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫዎችን በመጠቆም ላይ ናትም ይላሉ፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ሃይማኖት ጌታቸው በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን ፖለቲካዊ ለውጥ በተፈጠረ ቁጥር አጀንዳ ተቀባይና አጎብዳጅ ከመሆን ወጥተው ሀሳብ አመንጪ መሆን ይግባቸዋል ብለዋል። የክልል መገናኛ ብዙሃን ለአካበቢያቸው ወይም ለብሄራቸው የሚያዳሉ የአዘጋገብ ዝንፈቶች የሚታዩባቸው በመሆኑ ለለውጡ ስጋት እንደሆነ ገልጸው ችግሩን ለመቅረፍ ብዙሃንን በማቀራረብ ለሀገራዊ መግባባት እንዲሰሩ የሚያስችል የማዕቀፍ ወይም የፖሊሲ ትግበራ እንደሚያስፈልግም ገልጿል። የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቶች ሳይንሱን ከማስተማር ባሻገር የሙያ ብቃት የሚሰጡበት የጋዜጠኞች ማህበራት የሚጠናከሩበት ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለባቸውም  መምህር ሃይማኖት  ምክራቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም