ኢትዮጵያውያን ዳኞች በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚደረጉ የቅደመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ይመራሉ

130
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 ኢትዮጵያውያን ዳኞች በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚደረጉ የቅደመ ማጣሪያ ሁለት ጨዋታዎችን በመሐል ዳኝነት ይመራሉ። አህጉራዊው የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ከቀናት በኋላ በሚደረጉ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ይጀመራል። ህዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም የሚደረገው የሊቢያው አል ናስር እና የደቡብ ሱዳኑ አል-ሒላል ጁባ የሚያደርጉትን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በመሐል ዳኝነት እንደሚመሩ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ አስታውቋል። ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞች ትግል ግዛው እና በላቸው ይታየው ጨዋታውን በረዳት ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ጨዋታውን ይመራል። ህዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም በዚምባቡዌው ፕላቲኒየም እና በማዳጋስካሩ ሲናፕስ መካከል የሚደረገውን ጨዋታም በተመሳሳይ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በመሐል ዳኝነት ይመራዋል። ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞች ተመስገን ሳሙኤል እና ትግል ግዛው በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ጨዋታውን ይመሩታል። በቅደም ተከተል በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ እና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉት ጅማ አባ ጅፋር ከጅቡቲው ቴሌኮም እንዲሁም መከላከያ ከናይጄርያው ሬንጀርስ ይጫወታሉ። በአሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደ ጊዮርጊስ የሚመራው የአምናው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋር ህዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም በጅቡቲ ለሚያደርገው ጨዋታ 18 ተጫዋቾችን ይዞ ነገ ማምሻውን ወደ ስፍራው ያቀናል። የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ህዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደርጋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም