ቀጥታ፡

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከወጪ ንግድ የሚያገኘው ገቢ 35 ሚሊዮን ዶላር ደረሰ

አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከወጪ ንግድ የሚያገኘው ገቢ 35 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ። ኢንዱስትሪ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ውጭ መላክ ሲጀምር በዓመት አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያስገኝ ሲሆን ግቡን ለማሳካት የሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ተገልጿል። ኮሚሽኑ በአገሪቱ ካሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለሙያዎችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተቋማቱ የስራ እንቅስቃሴ ዙሪያ በአዲስ አበባ ውይይት እያደረገ ነው። በ350 ሄክታር መሬት ላይ 52 ሼዶችን የያዘው የሀዋሳ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ የገባው መጋቢት 2009 ዓመተ ምህረት ነበር። በፓርኩ ቢ ቪ ኤች የተባለውን የአሜሪካ ኩባንያ ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ ኩባንያዎች የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርት ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበያ እያቀረቡ መሆኑ ይታወቃል። የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በላይ ኃይለሚካኤል ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በየጊዜው ያሉበትን ችግሮች በመፍታት ከወጪ ንግድ የሚያገኘውን ገቢ እያሳደገ ነው። በስራ ላይ የሚሰማሩት ወጣቶች የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውን የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ ከትምህርት መጀመርና በቀን ስምንት ሰዓት የመስራት ልምዳቸው ዝቅተኛ መሆኑን ተከትሎ የሰራተኛ እጥረት ቢያጋጥምም በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል። ባለፈው ዓመት በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ተከስቶ የነበረው የሰራተኛ እጥረት በመቀነሱ በአሁኑ ወቅት በወር እስከ አራት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል። ከሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘው የወጪ ንግድ መጠን 35 ሚሊዮን ዶላር መድረሱ ውጤታማ የሚባል ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ ደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል። በመሆኑም የአገሪቱን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ለማሳደግ በሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ እየገመገምን አሰራራችንን የበለጠ እያዘመንን እንሄዳለን ብለዋል። በሁሉም ቦታዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት ስለማይቻል ባሉት ውጤታማ ስራ በመስራት ለሌሎች ፕሮጀክቶች ልምዱን ማሸጋገር የቀጣይ የቤት ስራችን ነው ብለዋል ኮሚሽነሩ። እቅዱን ከግብ ለማድረስ በፖሊሲ፣ በመሰረተ ልማትና በአገልግሎት አቅርቦት ደረጃ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በየደረጃው ባለው አካል እንዲሰሩ እናደርጋለን ብለዋል።                                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም