የኢትዮጵያ ቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ተጀመረ
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 ስምንት ክለቦች የሚሳተፉበት የ2011 ዓ.ም የወንዶች ሐበሻ ሲሚንቶ የቮሊቮል ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ከሚያካሄዳቸው መርኃ ግብር በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ውድድር በ2011 ዓ.ም ''ሐበሻ ሲሚንቶ ፕሪሚየር ሊግ'' በሚል ስያሜ እንደሚካሄድ ገልጿል። ዛሬ ውድድሩ በትንሿ ስታዲየም ሲጀመር በአምስት ዙር በተደረገ ጨዋታ መከላከያ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 3 ለ 2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል መጀመሩን የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። ነገ በትንሿ ስታዲየም ከጠዋቱ 3 ሰአት አዲስ አበባ ፖሊስ ከጣና ባህርዳር በ4 ሰአት ሙገር ሲሚንቶ ከመደወላቡ ዩንቨርሲቲ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ሶዶ ላይ ነገ ወላይታ ዲቻ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በእንግዳው ክለብ ጠያቂነት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ጠቁመዋል። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከ2005 ዓ.ም አንስቶ በሁለቱም ጾታዎች የፕሪሚየር ሊግ ውድድር እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በአሁኑ ሰአት ያሉትን አራት ክለቦች በመጨመር ውድድሩን ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ወላይታ ዲቻና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በቅደም ተከተል የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግና የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።