ኢትዮጵያ ውስጥ የጥጥ እርሻ ልማት ዘርፉ ፀጥታን ጨምሮ የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሙት መሆኑ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ውስጥ የጥጥ እርሻ ልማት ዘርፉ ፀጥታን ጨምሮ የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሙት መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 ኢትዮጵያ ውስጥ የጥጥ እርሻ ልማት ዘርፍ የፀጥታንና የሰው ኃይል እጥረትን ጨምሮ የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሙት መሆኑ ተገለፀ። የጥጥ አምራቾችና ምርቱን በጥሬ እቃነት የሚጠቀሙ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች እየገጠሟቸው ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በተናጠል ሳይሆን በቅንጅት መስራት አለባቸው ተብሏል። የችግሮቹን መኖር የተገነዘበው መንግስትም ችግሮቹን ለመፍታት የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑም ተገልጿል። ጥጥ አቅራቢዎችና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች በመካከላቸው ያለውን የሥራ ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉበት መንገድ ላይ የመከረ መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በውይይቱ ወቅት ሁለቱም ወገን ያሉባቸውን ችግሮች አንስተዋል። የባዳሀሞ የእርሻ ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ መሐመድ በእርሻ ማሳ ላይ የደረሰ ለጥጥ ምርት ለቀማና አረም መንቀል ስራ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጉልበት ሰራተኛ ይስፈልጋል፤ ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን ገልጸዋል። በዚህም የተነሳ አፋር ውስጥ ባላቸው የጥጥ እርሻ መሬት 20 ሺህ ኩንታል የደረሰ የጥጥ ምርት ቢኖርም "የደረሰውን ምርት ለመልቀም የሚያስችል የሰው ሃይል በመታጣቱ ምክንያት እስካሁን ተለቅሞ የተዳመጠው 7 ሺህ ኩንታል ምርት ብቻ ነው" ብለዋል። ምርቱ በፍጥነት ባለመሰብሰቡ ምክንያት ደግሞ በፀሐይና ዝናብ ለብልሽት እየተዳረገ እንደሆነም ተናግረዋል። "ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው በተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ ማሳሰቢያ የተሰጠ ቢሆንም ከመንግስት በኩል እስካሁን ምንም መልስ አላገኘሁም" ብለዋል። የመተማ ዩኒዮን የግብይት ክፍል ሃላፊ አቶ ክንዱ ወርቁ በበኩላቸው በመተማና ቋራ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ምርት በሚፈለገው ደረጃ ማምረት እንዳልተቻለ ገልፀው "በአካባቢው በሚነሱ ግጭቶች የደረሱ የጥጥ እርሻዎች እየተቃጠሉ ነው" ብለዋል። ባለው የፀጥታ ችግር ሳቢያ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የሚንቀሳቀሱት በስጋት መሆኑን ጠቅሰው ለጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጠ የሚፈለገውን የጥጥ ምርት ማግኘት እንደማይቻል አሳስበዋል። የብርሃኑ እርሻ ልማት ድርጅት ባለቤት አቶ ብርሃኑ ህሩይ በበኩላቸው በቤኒሻንጉል ክልል የሚያካሄዱት የጥጥ እርሻ ልማት የክልሉ አመራሮች በሚፈጥሩት ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ሳቢያ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደተሳናቸው ገልፀዋል። "እነዚህ አካላት እኛ ምርት እንድናመርት አይፈልጉም፤ ያመረትነውን ምርት ለምንፈልገው ድርጅት እንዳናቀርብ እክል እየደረሰብን ነው" ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል። ጉዳዩን እስከ ጠቅላይ ሚኒስተር ጽህፈት ቤት ድረስ ለማሳወቅ ጥረት መደረጉን የሚናገሩት ባለኃብቱ "ከአሜሪካ መጥቼ አገሬን ለማልማት ፍላጎት ቢኖረኝም በክልሉ አመራሮች እየደረሰብኝ ያለው ጫና እክል ሆኖብኛል" ብለዋል። የሰው ኃይል አጥረትንና የፀጥታ ችግርን የሚጋሩት ጥጥን በጥሬ እቃነት የሚጠቀሙ የጨርቃጨርቅ አምራች ድርጅቶች በበኩላቸው የጥጥ ጥራት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን አንስተዋል። ከእነዚህም መካከል የዓለም ገና ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ያሲን ገረሱ ከጥጥ እርሻ ልማት የሚገኘው ጥጥ ጥራት የጎደለው ከመሆኑ በላይ የሚቀርብበት ዋጋም ከፍተኛ መሆን ምርታቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆን እንዳደረገው ገልፀዋል። "መንግስት የጥጥ ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብና እንደሌሎች አገራት ለአምራቾች ድጎማ በማድረግ አቅማቸውን ቢያጎለብት መልካም ነው" ሲሉ አቶ ያሲን መክረዋል። የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ነጋሽ ጎሹ የተነሱት ችግሮች በየተናጥል ሳይሆን የጋራ ስለሆኑ መፈትሄ ለማበጀት ተቀራርቦ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው ያሳሰቡት። የጥጥ አምራቾች እና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ተነጣጥለው መኖር እንደማይችሉ በመገንዘብ "ከመወቃቃስ ተቀራርቦ በመነጋገርና በመወያየት የጋራ መግባባት ላይ መደረስና የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይገባል" ብለዋል። በሁለቱም አካላት በኩል የተነሱ ችግሮች ትክክል መሆናቸውን የጠቀሱት የኢትዮጵያ ጥጥ አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት ሼህ የሱፍ ዑመር በበኩላቸው ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በጋራ መስራት ካልቻሉ የዘርፉ እድገት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አስጠንቅቀዋል። "መንግስትም ላለፉት 10 ዓመታት ሲነገር ለቆየው ይህ የዘርፉ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ጣልቃ መግባት አለበት፤ ለሌሎቹ መስኮች ትኩረት እንደሰጠው ሁሉ ለጥጡ ዘርፍም ትኩረት መስጠት አለበት" ብለዋል። የማምረቻ ወጪ ከፍተኛ መሆን፣ የኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የጥጥ መዳመጫ መለዋዋጫ አቅርቦት ማነስና በተቀናጀ የግብይት ስርአት እጦት ሳቢያ እየተስፋፋ የመጣው የህገ ወጥ ደላሎች ተግባርም ሌሎቹ በውይይቱ የተነሱ ችግሮች ናቸው። የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት የጥጥ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ በበኩላቸው ችግሮቹ እንዲፈቱ የተለያዩ ጥረት አየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል። ችግሮቹን በሙሉ በአንድ ጊዜ ለመፍታት የሚያዳግት በመሆኑ ሁሉም የሚመለከተው አካል በጋራ ሊረባረብ ይገባልም ብለዋል። "የጸጥታውን ችግር ለመፍታት ከክልል ጸጥታ አካላት ጋር እየተጋገርን ነው፤ አሁን ግን ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ለሚመለከተው የመንግስት አካል እናሳውቃለንም" ሲሉም አስታውቀዋል። መንግስት በጥጥ ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት ያስችላል የተባለ የ15 ዓመት የጥጥ ልማት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ባለፈው ዓመት ወደ ሥራ ገብቷል።