በአዲስ አበባ ለሰባት ሺህ የጤና ባለሙያዎች ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ለሰባት ሺህ የጤና ባለሙያዎች ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ሊገነባ ነው
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 "አካንሊ" የተሰኘው የቱርክ የኮንስትራክሽን ኩባንያ አዲስ አበባ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ችግር ላለባቸው ሰባት ሺህ የጤና ባለሙያዎች ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ሊገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር አስታወቀ። የቤት ችግሩ የጤና ባለሙያዎች ካለባቸው የስራ ጫና ጋር ተደርቦ በሚሰሩት ስራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለባቸውና ለፍልሰት እየዳረጋቸው እንደሆነ ለኢዜአ ገልጸዋል። የመኖሪያ ቤቶቹ በሚገነቡበት አካባቢ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች፣ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎችና ሌሎችም የመዝናኛ ስፍራዎች የቤት ልማቱን ተከትሎ የሚገነባ ሲሆን አጠቃላይ ወጪውም ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተጠቁሟል። ለ10 ዓመታት በህክምና ዘርፍ አገልግሎት የሰጡት ዶክተር ዮናስ ሞገስ የራሳቸው የቤት ባለቤት መሆን እንዳልቻሉ ተናግረው፤ የስራው ባህሪ ከመንግስት የስራ ሰዓት ውጪ ሌሊትና በጠዋት የሚያስወጣ በመሆኑ ተከራይተው በሚኖሩበት ቤት ጭቅጭቅና እንግልት እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል። ባለሙያው ተጨማሪ ገቢ ፍለጋ የመንግስት የስራ ሰዓትን መሸራረፍ፣ በሞራል ማጣት ለታካሚው ጥራት ያለው አገልግሎት አለመስጠትና ሌሎችም ችግሮች በህክምናው ላይ የሚከሰትበት አጋጣሚ ሰፋ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም የተነሳ የህክምና ባለሙያው አገሩን ከማገልገል ይልቅ የተሻለ ክፍያ ወዳለባቸው አገሮች በብዛት እየፈለሰ እንደሚገኝ የተናገሩት። ሌላኛው የህክምና ባለሙያ አቶ ስንታየሁ አሰፋ እንደሚሉት መንግስት የህክምና ባለሙያው በየጊዜው የሚያነሳውን ችግር ለመፍታት ቸልተኝነት አሳይቷል። "በተለይ የቤት ችግር ለነገ የሚባል አይደለም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አልፎ አገርንና ህዝብን በማገልገል ላይ ላለው ባለሙያ ትኩረት መሰጠት አለበት" ይላሉ። ሀኪሞቹ አሁን ሊጀመር የታሰበውን የቤት ግንባታ አስፍቶ ሁሉም ባለሙያ የቤት ልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚደረገው ጥረት መፋጠን አለበት ብለዋል። የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቺስ ማሞ እንዳሉት፤ በቅርቡ የቱርክ ካምፓኒ የመኖሪያ ቤት ችግር ላለባቸው ሃኪሞች በራሱ ወጪ ቤት ገንብቶ በረጅም ጊዜ ክፍያ ማስተላላፍ ስምምነት አድርጓል። ግንባታው በመጪዎቹ ሶስት ወራት የሚጀመር ሲሆን ግንባታውን ከአምስት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አከናውኖ ለሰባት ሺህ የጤና ባለሙያዎች እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል። ግንባታው የሚካሄደው በየካ ክፍለ ከተማ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ካምፓኒው መመደቡን ዶክተር ገመቺስ ተናግረዋል። የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎችና ሌሎችም የመዝናኛ ስፍራዎች የቤት ልማቱን ተከትሎ ይገነባሉ አጠቃላይ ግንባታዎቹ በሁለት ክፍሎች ተከፍሎ ነው የሚከናወነው። ባለሙያው ቤቱን በ20 ዓመት ከፍሎ እንዲጨርስ የሚያስችል እቅድ እንዳለ ተናግረው የቤት ልማት ፕሮግራሙም ወደ ተለያዩ ክልሎች የማስፋት ስራ ለመስራት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ዋጋው በአገሪቱ ሪል ስቴቶች ገንብተው ለነዋሪው ከሚሸጡት የቤት ዋጋ 25 በመቶ ቅናሽ እንደሚኖረው ዶክተር ገመቺስ ጠቁመዋል። በቀጣይም ሁሉንም የህክምና ባለሙያዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍላጎት እንዳለ ተጠቁሟል።