ክለቦች በወቅቱ ባለመመዝገባቸው ምክንያት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ሊጀመር አልቻለም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ክለቦች በወቅቱ ባለመመዝገባቸው ምክንያት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ሊጀመር አልቻለም ተባለ
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 የከፍተኛ ሊግ የእግር ኳስ ክለቦች በወቅቱ ባለመመዝገባቸው የ2011 ዓ.ም ውድድር በተያዘለት መርኃ ግብር ሊጀመር እንዳልቻለ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። ውድድሩን በተቀመጠው መርኃ ግብር ለማስጀመር ተወዳዳሪ ክለቦች አስፈላጊውን መስፈርት በወቅቱ እንዲያሟሉ በተደጋጋሚ ማሳወቁን ፌዴሬሽኑ ገልጿል። ሆኖም ክለቦቹ በወቅቱ ባለመመዝገባቸው የተነሳ ውድድሩ በተቀመጠው መርሃ ግብር መሠረት ሊጀመር እንዳልቻለ ነው ፌዴሬሽኑ ያመለከተው። ተወዳዳሪ ክለቦቹ መስፈርቱን ያላጠናቀቁበትን ምክንያት ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ እንዲያሳውቁ ፌዴሬሽኑ ጠይቋል። ክለቦቹ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ምዝገባውን የማያከናውኑ ከሆኑ በተገኙት ክለቦች ብቻ ውድድሩ የሚጀመር መሆኑን የሊግ ኮሚቴው አስታውቋል። ክለቦቹ እስካሁን ያላሟሉት መስፈርት የመመዝገቢያ ክፍያ አለመክፈላቸው እንደሆነ ይገለፃል። የከፍተኛ ሊግ ውድድር ህዳር 16 እና 17 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀመራል ቢባልም ክለቦች የሚጠበቅባቸውን መስፈርት ባለሟሟላታቸው ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን ወደ ኅዳር 22 እና 23 ቀን 2011 ዓ.ም መቀየሩም ታውቋል። በክለቦች የምዝገባ ክፍያ መዘግየት ምክንያት የከፍተኛ ሊጉ ውድድር አምናም በተመሳሳይ በተቆራረጠ ሁኔታ ዘግይቶ እንደተጀመረ ይታወሳል። የ2011 ዓ.ም አንደኛ ሊግ (ብሔራዊ ሊግ) በተመሳሳይ ችግር ውድድሩ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙም ተገልጿል። የከፍተኛ ሊግና አንደኛ ሊግ (ብሔራዊ ሊግ) ክለቦች በወቅቱ ምዝገባ ባለማካሄዳቸው ምክንያት ውድድሮች ዘግይተው ሲጀመሩ ይስተዋላል።