አፍላቶክሲንና የጥራት ችግሮች ወደ ውጭ በሚላኩ የግብርና ምርቶችን ገበያ እያሳጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አፍላቶክሲንና የጥራት ችግሮች ወደ ውጭ በሚላኩ የግብርና ምርቶችን ገበያ እያሳጣ ነው
አዲስ አበባ ህዳር 15/2011 አፍላቶክሲንን (ሻጋታ) ጨምሮ የጥራት ደረጃቸው በላቦራቶሪ ሳይፈተሽ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች የገበያ ተቀባይነት እያጡ መሆኑ ተገለጸ። የምርቶችን የጥራት ደረጃ የሚፈትሹ ማሽኖች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም። አፍላቶክሲን ወይም ሻጋታ አስፓሪጊለስ ፍላቨስና አስፓሪጊለስ ፓራክቲከስ በተባሉ የፈንገስ አይነቶች የሚመጣና ምግብን የሚመርዝ የተህዋሲያን ውጤት ነው። የአፍላቶክሲን ዓይነቶች ቢ1፣ ቢ2፣ ጂ1ና ጂ2 ሲሆኑ በተለይ ቢ1 የተባለው አደገኛ፣ መርዛማና ቶሎ ሊገድል የሚችል መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል። በዓለም ላይ 30 በመቶ ሚሆነው የጉበት ካንሠር በአፍላቶክሲን መርዝ የሚከሰት ሲሆን የኩላሊት ካንሠር፣ የእድገት መቀነስና የደም መፍሰስ ችግሮችንም ያስከትላል። በተለይ በቆሎ፣ ኦቾሎኒ፣ የዛፍ ፍሬና የእንስሳት ውጤቶች በከፍተኛ ሁኔታ የፈንገሱ ተጠቂ ሲሆኑ ሌሎች ምርቶች ላይም በየደረጃው ይከሰታል። አፍላቶክሲን ወይም ሻጋታ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግብርና ምርቶች በዓለም ገበያ ተቀባይነት እንዲያጡ ማድረጉን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የድህረ ምርት ባለሙያ አቶ አውራሪስ አስፋው ˝ትልቁ ጉዳት ደግሞ አሁን ኤክስፖርት የምናደርጋቸው ሰብሎች ላይ በተለይ አውሮፓ ገበያ ላይ እኛ ማቅረብ አንችልም፤ ምክንያቱም ከፍተኛ ኮንታሚኔትድ የሆነ ነው፤ ስለዚህ በኤክስፖርት ሰብሎች ላይም ሆነ በጤና ላይ ችግር አለው፣ በአፍላቶክሲን የተጠቁ ሰብሎችን ወደ ገበያ በሚቀርቡበት ጊዜ ጥራታቸው አነስተኛ ስለሆነ ''ብለዋል፡፡ በሚኒስቴሩ የእጽዋት ኳረንታይል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ በለጠ ሞገስ እንዳሉት ቀደም ሲል ጥራጥሬ በብዛት ይገዙ የነበሩት የአውሮፓ አገሮች፣ ህንድና ፓኪስታን በነፍሳት ተባይና በሽታ እንዲሁም ከአደገኛ የአረም ዝርያዎች ነፃ መሆኑን ማረጋገጫ ባለማግኘታቸው መግዛት ማቆማቸውን ተናግረዋል። ከፍተኛ እርጥበት፣ በማሳና በጎተራ የነፍሳትና ተባዮች መከሰት፣ ምቹ ያልሆነ ማከማቻና ማጓጓዣ ለፈንገሱ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል። የአፍሪካ ህብረት አፍላቶክሲንን ከአፍሪካ ለማጥፋት እኤአ ከ2015 እስከ 2018 በማላዊ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ፣ ጋምቢያና ኡጋንዳ ባዮ ኮንትሮል (አፍላሴፍ) የተባለ ፕሮጀክት ነድፎ ወደ ስራ ገብቷል። ይህ ፕሮጀክት በየአገሮቹ የአፍላቶክሲን አይነቱን በመለየት ራሱ ፈንገሱን በመርጨት ከ80 እስከ 90 በመቶ መከላከል ተችሏል። ይህን ፕሮጀክት ከ2018 ጀምሮ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና ቤኒን ወደ ትግበራ ለማስገባት ቅድመ ዝግጅቶች መጀመራቸውን አቶ አውራሪስ ይናገራሉ። ይህ ፕሮጀክት ገና ሂደት ላይ ያለ በመሆኑ እየተባባሰ ለመጣው ችግር አፋጣኝ መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ የማይታሰብ በመሆኑ ለአምራቹና ለተጠቃሚው ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጥ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል። የእጽዋት ኳረንታይል ከፍተኛ ባለሙያው አቶ በለጠ ሞገስ እንደሚሉት፤ አብዛኞቹ የግብርና ምርቶችን የሚገዙ አገሮች ምርቶቹ ከተባይ ነጻ መሆናቸውን በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ማስረጃ ይፈልጋሉ። ይህ የላቦራቶሪ ማረጋገጫ አለመኖር ደግሞ ችግሩን የበለጠ አባብሶታል። የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ እንደመሆኑ በየዓመቱ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሬ ካለማስገኘቱ ባለፈ ምርቶች ላይ እያጋጠመ ያለው የጥራት ችግር ሌላ ፈተና ከሆነ ሰነባብቷል። በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተኬ ብርሃነ ድርጅቱ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ በፍቃደኝነትና በአስገዳጅነት ላይ የተመሰረተ የጥራት ማረጋገጫ ፍተሻ እያደረገ እንደነበር ገልጸዋል። በተለይ የገቢና ወጪ ምርቶች ላይ ናሙና በመውሰድ በተቀመጠለት የጥራት ደረጃ መመረት አለመመረቱን የላቦራቶሪ ፍተሻ ይደረጋል። ይሁንና ቀደም ሲል በተለያዩ ምርቶች ላይ ያለውን የአፍላቶክሲን መጠን ይፈትሽበት የነበረው ማሽን ካለፈው ክረምት ጀምሮ በብልሽት ምክንያት አገልግሎት መስጠት ማቆሙን ተናግረዋል። ማሽኑን ለመጠገን በአገር ውስጥ ባለሙያ ካለመኖሩ ባለፈ ከውጭ ባለሙያና መለዋወጫ መሳሪያዎችን ለማስመጣት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የግብርና ምርቶች በላቦራቶሪ እጥረት ምክንያት ጥራታቸው ሳይረጋገጥ ወደ ውጭ ገበያ እየተላኩ ተመልሰው እየመጡ ነው። የአገሪቷ የወጪ ንግድ ከአመት አመት እያሽቆለቆለ የመጣ ቢሆንም በግብርና ሚኒስቴርም ሆነ በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የምርት ጥራት የፍተሻ ላቦራቶሪዎች አለመኖራቸው ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልተሰጠው አመላካች ነው። በኢትዮጵያ ከፍተኛው የአፍላቶክሲን መጠን በፐር ሚሊየን በቆሎ 95፣ ኦቾሎኒ 11ሺህ 865፣ ማሽላ 63፣ ቅመማ ቅመም 252፣ ገብስ፣ ጤፍና ስንዴ 26 እንዲሁም ወተት 416 ነው።