ቀጥታ፡

በየጊዜው ለሚስተዋለው የነዳጅ እጥረት ምክንያቱ ህገ-ወጥ ንግድ መሆኑን ተጠቃሚዎች ገለጹ

አዲስ አበባ  ህዳር 14/2011 በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚስተዋለው የነዳጅ እጥረት ምንጭ ከህገ-ወጥ ነጋዴዎች ጋር በተያያዘ የሚፈጠር በመሆኑ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ተጠቃሚዎች ገለጹ። የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በበኩሉ በህገ-ወጥ መንገድ የነዳጅ ንግድ እንቅስቃሴ እንዳለ ማረጋገጡን አስታውቋል። ድርጅቱ ባካሄደው ጥናት በአዲስ አበባ በርካታ ህገ-ወጥ የነዳጅ መሸጫ ቦታዎች መኖራቸውም ተደርሶበታል። በአዲስ አበባ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገረቻቸው ነዳጅ ተጠቃሚዎች እንዳሉት በነዳጅ ማከፋፈልና እደላ ተግባር የተሰማሩ የመንግስት ሰራተኞችም የተለየ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ በዚህ ህገ-ወጥ ሥራ ከተሰማሩት መካከል ይገኙበታል። በየጊዜው ለሚፈጠረው የነዳጅ እጥረት ምክንያት የሆነውን ይህንን ህገ-ወጥነት መንግስት ሊገታው አንደሚገባም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ ያሳሰቡት። በአሁኑ ወቅትም የነዳጅ እጥረት እየተስተዋለ መሆኑን በማከል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ መኮንን ኪዳኔ እንደተናገሩ ህገ ወጥ የነዳጅ ንግድን ለመከላከል የሚያስችል የቁጥጥር ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል ይላሉ። በታክሲ አገልግሎት የተሰማራው ወጣት ይበልጣል አበባው በበኩሉ "እኔና የስራ ባልደረቦቼ በአሁኑ ሰዓት በቤንዚን እጦት ስራችንን መስራት ተስኖናል፣ መንግሰት በእነዚህ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል"  ብሏል። የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማሪያም ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በህገ-ወጥ መንገድ ነዳጅን የማሸሽ ስራ እንደሚስተዋል አረጋግጠዋል። ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ  በተካሄደው ክትትል ከከተማዋ ወደተለያዩ አካባቢዎች ሊወጣ የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ተይዘዋል። ሆኖም ግን ተግባሩን በፈፀሙት ላይ ተገቢው እርምጃ አልተወሰደም፤ ምክንያቱ ደግሞ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የህግ ስርዓት ክፍተት አለ  ያሉት አቶ ታደሰ ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ስለሚሻ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባልም ሲሉ ያሳስባሉ። "በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ጉዳይ ለስኳርና የምግብ ዘይት የሚደረገውን ያህል ክትትል እንኳን እያገኘ አይደለም፤ ዘርፉ ባለቤት አልባ እስኪመስል ድረስ ህገ-ወጥ ንግዱ ተስፋፍቷል፤ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ እጅግ አሳሳቢ ስለሚሆን የሚመለከትን አካላት በጋራ ልንሰራ ይገባል" ብለዋል። አርሳቸው እንደሚሉት በከተማዋ በርካታ ህገ-ወጥ የነዳጅ መሸጫ ቦታዎች መኖራቸውን በነዳጅ አቅራቢ ድርጅቱ አራት ቡድኖች በተደረገ  ክትትል ተደርሶባቸዋል። በእነዚህ ቦታዎች ነዳጅ የሚሸጠው በህግ ከተተመነው ዋጋ እስከ 44 በመቶ ጭማሪ በማድረግ እንደሆነም ጥናቱ ያሳያል ብለዋል። በጉዳዩ ላይ በቀጥታ የሚመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ምላሽና ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጥ ዘንድ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘጋቢ ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት ከውጭ አገራት ለምታስገባው ነዳጅ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድባለች። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደአገር ቤት የሚገባው ይህ ነዳጅ በተገቢ ቁጥጥርና ክትትል ተጠቃሚው ዘንድ እንዲደርስ ካልተደረገ በህገ-ወጥ መንገድ የሚካሄደው እንቀስቃሴ አገራዊ ኢኮኖሚውን እንደሚጎዳው ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የሚናገሩት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም