በትግራይ ቋንቋዎችን ለማበልጸግ የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው... የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ቋንቋዎችን ለማበልጸግ የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው... የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት
መቀሌ ህዳር 14/2011 በትግራይ የሚነገሩ ቋንቋዎችን ለማበልጸግ የተደረጉ ጥረቶች ሊበረታቱ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አስታወቀ። በትግራይ ክልል በሚነገሩ የተለያዩ ቋንቋዎች ላይ አተኩሮ የሚመክር አገር አቀፍ ሲምፖዚየም በመቀሌ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል። በሲምፖዚየሙ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሐጎስ አብረሃ እንዳሉት በክልሉ የሚነገሩ ቋንቋዎችን በስነ ጽሁፍ፣ በስነ ቃልና በስነ ልሳን ለማበልጸግ የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው። በክልሉ የሚነገሩ የትግረኛ፣ ሳሆኛና ኩናምኛ ቋንቋዎችን ለማበልፀግ ባለፉት ዓመታት አገር አቀፍ ሲምፖዚየም በማዘጋጀትና ጥናታዊ ጽሑፎችን በማሳተም ለአንባቢያን ለማድረስ ጥረት ተደርጓል። በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ቋንቋዎችን ለማበልጸግ የጀመሩት ምርምርና ጥናት የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል። የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል ተክሉ " ኤጀንሲው በሦስቱም ቋንቋዎች የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት አድርጓል" ብለዋል። የዘርፉ ምሁራንን በመጋበዝና በርካታ የምርምር መድረኮችን በማዘጋጀት በቋንቋዎቹ አጠቃቀም የሚታዩ ጉድለቶችን ለማስተካከል ሲሰራ መቆየቱንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በ35 የዘርፉ ምሁራን የተካሄዱ 60 ጥናታዊ ጽሁፎችና 51 አጫጭር ጽሁፎች ታትመው ለቋንቋው ተጠቃሚዎች እንዲሰራጩ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ የሲምፖዚየሙ ተሳታፊና የኩናማ ብሔረሰብ አባል አቶ መስፍን ኬኙ በበኩላቸው የኩናምኛ ቋንቋ ከንግግር አልፎ ለስርዓተ ትምህርት አገልግሎት መዋሉ ለቋንቋው ትኩረት መሰጠቱን ያሳያል ብለዋል፡፡ የኢሮብ ብሄረሰብ አባል መምህር ዝግታ ሀድጉ በበኩላቸው በሳሆኛ ቋንቋ የመማርና የመዳኘት እድል በመገኘቱ የብሔረሰቡ አባላት በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ በመቀሌ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚቆየው አገር አቀፍ ሲምፖዚየም 24 ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን ከከፍትኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከኪነጥበብ ባለሙያዎችና ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተወከሉ ከ96 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።