በድሬዳዋ አስተዳደር መደበኛ እንቅስቃሴ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አስተዳደር መደበኛ እንቅስቃሴ ቀጥሏል
ድሬዳዋ ህዳር 14/2011 በድሬዳዋ አስተዳደር ሰሞኑን ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች መደበኛ እንቅስቃሴ መቀጠሉን ፖሊስ አስታወቀ። በአስተዳደሩ አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር ሚናቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን የሰጡ ነጋዴዎችና ወጣቶች ተናግረዋል፡፡ በአስተዳደሩ በተለይም በድሬዳዋ ከተማ ላለፉት አራት ቀናት ችግር የተፈጠረባቸው አካባቢዎች ዛሬ ሙሉ ለሙሉ ወደ መረጋጋት ተመልሰዋል።መደበኛና የንግድ እንቅስቃሴም ወደ ወትሮ ሁኔታ ተመልሷል፡፡ የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ሳጅን ባንተአለም ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት ሰሞኑን በአስተዳደሩ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በፀጥታ አካላትና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወደ መረጋጋት ተመልሷል፡፡ የአስተዳደሩና የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት አባላት የፈጠሩት ጥምር ኃይል ወጣቶችን በማሳተፍ ባደረገው እንቅስቃሴ በተለይ ችግሩ በተደጋጋሚ በሚፈጠርባቸው አካባቢዎች ሰላምን በአስተማማኝ መንገድ ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በግጭቱ በጠፋው ሕይወትና ለአካል ማጉደል ተግባራት እንዲሁም ሃብትና ንብረት በማውደም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለፍርድ በማቅረብም የሕግ የበላይነት እየተረጋገጠ ይገኛል ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ የጀመረውን ሥራ እንዲያጠናክር ዋና ሣጂን ባንተአለም ጠይቀዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ በበኩላቸው በአስተዳደሩ በተከናወነው የተቀናጀ ተግባር በገጠርና በከተማ መረጋጋት መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የማኀበረሰብና ባህላዊ መሪዎች ያካተተ ኮሚቴ ተቋቁሞ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና መረጋጋትን ለመፍጠር ጥረቱ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮችና በዘላቂ ሰላም እሴት ግንባታ ላይ በየደረጃው የሚገኙ ወጣቶች የሚሳተፉበት ውይይት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡ የቀፊራ አካባቢ የአትክልት ነጋዴ ወይዘሮ ፋጡማ ሙመድ ምንነቱ ባልታወቀ ሰላማቸው ታውኮና ገበያቸው ተዘግቶ እንደነበር ተናግረዋል። ''ሰላም ከሌለ ልጆቼን የማሳድግበት ሥራ ይቆማል። ሁሉም በየቤቱ ይቀመጣል። ይህ እንዳይሆን ከፀጥታ አካላት ጋር ሆነን ሰላማችን መጠበቅ ይገባናል'' ብለዋል፡፡ በእንጨትና በብረታ ብረት ሥራ የሚተዳደሩትና 10 አባላት ያሉት የነወጣት መስፍን አየለ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት መስፍን ሰላም የሁሉም ሥራ መነሻና መድረሻ ሰላም በመሆኑ ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፡፡ ሰላምን በማደፍረስ የሚጎዳ እንጂ፤ የሚጠቀም አለመኖሩን አውቆ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም እንዲረባረብ ጠይቋል፡፡