ቤተክርስቲያኗ በጌዴኦና ጉጂ ሕዝቦች መካከል የተጀመረውን የሰላም ግንባታ ለማጠናከር እየሰራች ነው- ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ፡፡ - ኢዜአ አማርኛ
ቤተክርስቲያኗ በጌዴኦና ጉጂ ሕዝቦች መካከል የተጀመረውን የሰላም ግንባታ ለማጠናከር እየሰራች ነው- ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ፡፡
ዲላ ህዳር 14/2011 የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በጌዴኦና ጉጂ ህዝቦች መካከል የተጀመረውን የሰላም ግንባታ ለማጠናከር እንደምትሰራ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ገለጹ፡፡ ቤተክርስቲያኗ ከካቶሊክ እርዳታ ድርጅት "ሲ.አር.ኤስ" እና "ወርልድ ቪዥን" ጋር በመተባበር የጌዴኦና የጉጂ ህዝቦች የሰላም ግንባታ ሂደት ባለድርሻ አካላት ጋር የአጋርነት የምክክር መድረክ በዲላ ከተማ አካሂዳለች፡፡ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት "ለዘመናት አብረው በኖሩ ህዝቦች መካከል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት የብዙ ሰዎች ሕይወት በመጥፋቱ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀላቸው እንዲሁም ንብረት በመውደሙ እጅግ አዝነናል" ብለዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗ ችግሩ ከተከሰተ ጀምሮ ከግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የምግብ፣የመጠለያና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ተናግረዋል፡፡ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አባ ገዳዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣የፖለቲካ መሪዎችና ባለድርሻ አካላት ያደረጉትን ያላሰለሰ ጥረት አድንቀዋል፡፡ የተጀመረው የሰላም ግንባታ ሥር እንዲሰድና ማህበራዊ ትስስሩ ወደነበረበት እንዲመለስ ቤተክርስቲያኗ ከአጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደምትሰራም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን መምራት የሚችሉ፣ በመካከላቸው ችግሮች ሲፈጠሩም ተመካክረው በራሳቸው የመፍታት ጥበብ ያላቸው ታላቅ ሕዝቦች ናቸው ብለዋል፡፡ "በቅርብ ጊዜያት እየታየ ያለው መከፋፈልና ግጭት እንዲሁም በጠላትነት መተያየት የእኛ ታሪክ ያልሆነ የሚያሳፍር ተግባር ነው" ሲሉ ተናግረዋል ፡፡ ኢትዮጵያ በበርካታ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶች የበለጸገች ሀገር መሆኗን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ፣ ሕዝቦቿ ለሌሎች አገሮች አርአያ መሆናቸውን መዘንጋት እንደሌለበትም አስታውሰዋል ፡፡ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም ግንባታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ማሞ ወጀጋ "ፈጣሪ በልዩነት የፈጠረን በዚህ ምክንያት እርስ በእርሳቸን ልንገፋፋ ሳይሆን፤ ተደጋግፈንና ተከባብረን አብረን እንድንኖር ነው" ብለዋል ፡፡ የሐሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወደ ሁከትና ብጥብጥ አድገው ለሰዎች ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም ምክንያት ከመሆናቸው አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባም አመልክተዋል። ጉባዔው በአካባቢው አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው ከምዕራብ ጉጂ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣የአገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ አመራሮች የሚሳተፉበት ቋሚ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗ እያሳየችው ያለው መነሳሳት ጉባዔውን ጥረት ወደፊት እንደሚያራምድም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ በበኩላቸው ጌዴኦና ጉጂ የጠበቀ ባህላዊና ማህበራዊ ትስስር ያላቸው ሕዝቦች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ በግጭቱ ወቅት አንዱ የሌላውን ብሔር በማስጠለልና ከጥቃት በመከላከል ያሳዩትን አንድነት በማሳያነት የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ አካባቢውን የሰላም ቀጠና ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗ ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ አንጻር የጀመረችው እንቅስቃሴ ተሞክሮ እንደተገኘበትም ተናግረዋል፡፡ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ይመኑ ዳካ "አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እድሉ ከእጃችን ሳይወጣ ችግሩ ዳግም እንዳያገረሽና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ተባብረን መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል ፡፡ የሃይማኖት ተቋማትም የጀመሩትን ጥረት እንዲቀጥሉም አቶ ጠይቀዋል ፡፡ ቤተክርስቲያኗ ከካቶሊክ እርዳታ ድርጅት "ሲ.አር.ኤስ" ጋር በመተባበር ግጭቱ ከተከሰተ ጀምሮ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያለው የመጠለያ፣ የቁሳቁስና የምግብ ድጋፍ እያደረገች መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል ፡፡ "የጋራ ጥረት ለዘላቂ ሰላም" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ብጹዓን የቤተክርስቲያኗ አባቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣የተራድኦ ድርጅት ተወካዮች፣ የአመራር አካላትና የአገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል፡፡