ቀጥታ፡

የኖርዌይ መንግስት በኢትዮጵያ ለሚካሄድ የስነ-ተዋልዶ ጤና መርሃ ግብር ማስፈፀሚያ የ11 ነጥብ 3 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ህዳር 14/2011 የኖርዌይ መንግስት ለኢትዮጵያ የ11 ነጥብ 3 ሚሊዬን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ። የገንዘብ ድጋፉ በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት እና እና የስነ-ህዝብ ጉዳይ ጽህፈት ቤት አማካኝነት ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ለሚተገበረው የስነ ተዋልዶ ጤና መርሃ ግብር ማስፈፀሚያ የሚውል ነው። መርሃ ግብሩ  በወሲባዊና የስነ-ተዋልዶ ጤና፣ ኤይ.አይ.ቪ/ ኤድስ፣ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃትና ጎጂ ልማዶችን በመከላከል ተግባር ጥራት ያለው መረጃን፣ የድጋፍ አገልግሎትና የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ ያተኩራል። መርሃ ግብሩ ከ10 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አዋቂዎችና ወጣቶች ላይ እንደሚያነጣጥርም ተመልክቷል። በጉዳዩ ዙሪያ ቁልፍ ኃላፊነት ያላባቸውን የመንግስት ተቋማትና ሚኒስቴሮች፣ በወጣቶች የሚመሩ ድርጅቶች፣ ወላጆችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች አቅምን ማጠናከርም የመርሃ ገብሩ ዓላማ መሆኑ ተገልጿል። መርሃ ግብሩ በአፋር፣ በአማራ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልሎችና በአዲስ አበባ አስተዳደር በተመረጡ 20 ወረዳዎች የሚጀመር ሲሆን በቀጣይም በአገር አቀፍ ደረጃ ይተገበራል ተብሏል። በስምምነት ስነ ስርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ምረቴ ሉንዴሞ በመርሃ ግብሩ ሴቶችና ልጃገረዶች እርግዝናቸውን በእቅድ መወሰን እንዲችሉ፣ ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ እንዲያጠናቅቁና በስራ ላይ እንዲሳተፉ ያግዛቸዋል። ማስቻል ነው ብለዋል። መርሃ ግብሩ ተግባራዊ የሚሆነው የተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችንና የክልል ቢሮዎችን ጨምሮ በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የሚመለከታቸው አካላት አጋርነት ነው። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ ህዝብ ጉዳይ ፅህፈት ቤት የኢትዮጵያ ተወካይ ቤቲና ማስ መርሃ ግብሩ ሴቶችና ወጣቶች ስለ ወሲባዊና ስነ-ተዋልዶ ጤንነት መረጃና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወሰኑ ያስችላቸዋል ብለዋል። በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ጂሊያን ሜልሶፕ በበኩላቸው  መርሃ ግብሩ በተለይም ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች ውጤታማ የሆነ አዋቂ ዕድሜ ሽግግር እንዲኖራቸው እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም