መቀሌን ለኑሮ ምቹና ጽዱ ለማድረግ ለጽዳትና ውበቷ የተለየ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል- ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
መቀሌን ለኑሮ ምቹና ጽዱ ለማድረግ ለጽዳትና ውበቷ የተለየ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል- ነዋሪዎች
መቀሌ ህዳር 14/2011 መቀሌን ለኑሮ ምቹና ጽዱ ለማድረግ ለጽዳትና ውበቷ የተለየ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ የከተማው ነዋሪዎች አሳሰቡ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት ከተማውን በሁለንተናዊ መልኳ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን የጽዳትና ውበት ሥራዎችን ከሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች የማይተናነስ ትኩረት መስጠት ያሻል። ወጣት አረጋይ አብርሃ በከተማው ውስጥ የጽዳት ጉድለቶች የሚከሰቱት የግል ንፅህናና የአካባቢ ጽዳት ከቤተሰብና ከቤት ይጀምራል የሚለው አስተሳሰብ ውስጥ ባለመስረጹ መሆኑን ይገልጻል። ለዚህም ለውበትና የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ በየዓመቱ በሚተከሉ ችግኞች ላይ ተቆርጠው መጣላቸውን እንደ አንድ አብነት ያነሳሉ። በየቦታው ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻን ተጥሎ ማየት የተለመደ ነው ያለው ወጣት አረጋይ፣በግድየለሽነት ድርጊቱን የሚፈጽሙ ግለሰቦችና አካላት ተጠያቂ ማድረግ ይገባል ብሏል። በየቦታው የሚጣሉ ቆሻሻ የከተማውን ውበትና ፅዳት ከማበላሽት ባለፈ ለአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት(አተት)ና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ጠንቅ እየሆኑ መምጣታቸውን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ጤና መኮንን አቶ ዓለምሰገድ አባይ ናቸው። ከተማውን የማስዋብና የማጽዳት ሥራው ከመኖሪና ቤትና ከትምህርት ቤት ሊጀምር ይገባል ብለዋል። አቶ በየነ ይልማ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው በከተማው የመሠረተ ልማት ተቋማትን በመዘርጋት ብቻ ዕድገቷን ማረጋገጥና ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ማፍራት እንደማይቻል ይናገራሉ።ይህም የሚሳካው ''ለከተማው ውበትና ጽዳት መጠበቅ ልዩ ትኩረት ስንሰጥ ነው''ብለዋል። ለተግባራዊቱም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣አመራሮችና ህዝባዊ ማህበራት በተቀናጀ መንገድ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ምክራቸውን ይለግሳሉ። የመቀሌ ከተማ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረሚካኤል እኑን ጉዳዩን አስመልክተው ከተማውን በየዓመቱ ከ13 ሺህ በላይ ችግኞች ቢተከሉም፤ ለእንክብካቤው የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ችግኞች እንደሚደርቁ ተናግረዋል። ነዋሪዎች ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ከቤታቸው ክልል ከ20 እስከ 50 ሜትር የሚገኘውን የማጽዳት ኃላፊነት እንደተሰጣቸው የሚደነግግ ደንብ መውጣቱን አስረድተዋል። የከተማ ውበትና ጽዳት ጉዳይ ባለድርሻ አካላትንና የኅብረተሰቡ ተሳትፎ የሚጠይቅ እንጂ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ኃላፊው፣ ነዋሪዎች በተግባር የከተማውን ገጽታ ለመቀየር እንዲተጉ አሳስበዋል። መቀሌ 500ሺህ ነዋሪዎች ያሏትና ከሰሜን ኢትዮጵያ ታላላቅ ከተሞች አንዷ ናት።