የተቋረጠውን ጸገዴን ከከተማ ንጉስ ጋር የሚያገናኝ የአስፋልት መንገድ ለመክፈት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተቋረጠውን ጸገዴን ከከተማ ንጉስ ጋር የሚያገናኝ የአስፋልት መንገድ ለመክፈት እየተሰራ ነው
መቀሌ ህዳር 14/2011 የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ያቋረጠው ጸገዴ ወረዳን ከከተማ ንጉስ ጋር የሚያገናኘው የ22 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ለመክፈት የጥገና ስራ ተጀመረ። መስመሩ አገልግሎቱን ያቋረጠው ባለፈው ክረምት የጣለው ዝናብ ባስከተለው ከፍተኛ ጎርፍ መንገዱ ተሰናነጣጥቆና ተንሸራቶ በመፍረሱ እንደሆነ የጸገዴ ወረዳ የኮንስትራክሽን መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሃፍቶም ተመስገን ገልጸዋል። የመንገዱ ጥገና በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የጎንደር ዲስትሪክት አማካኝነት ከህዳር 10/2011 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። በባለስልጣኑ የጎንደር ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም አበራ በበኩላቸው ፣ በጎርፍ ምክንያት የተበላሸው የአስፋል መንገዱ ንጣፎች በማሽን በመጥረግ በአዲስ መልክ በጥራት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ለጥገና ስራው አስፈላጊ የሆኑት ማሽኖች በማሰማራት የጥገና ስራው እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው "የመንገድ ጥገናው በሁለት ሳምንት ውስጥ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲጀምር ይደረጋል "ብለዋል። ባለፈው ወር መግቢያ ላይ መንገዱ በመበላሸቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸው የከባድ ተሽከርካሪ ባለቤቶችና ነጋዴዎች መግለጻቸውና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የጥገና ስራ በቅርብ እንደሚጀመር ማሳወቁን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።