በአዲስ አበባ የቀበሌ መኖሪያ ቤት አሰጣጥ ሂደት የፍትሃዊነት ጥያቄ አስነስቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የቀበሌ መኖሪያ ቤት አሰጣጥ ሂደት የፍትሃዊነት ጥያቄ አስነስቷል
አዲስ አበባ 14/2011 በአዲስ አበባ የቀበሌ መኖሪያ ቤት አሰጣጥ ሂደት የፍትሃዊነት ጎደለው ነው ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ወይዘሮ የሺ ማርዬ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በሚገኝ አንድ ክፍል የግለሰብ መኖሪያ ቤት ተከራይተው ለ28 ዓመታት ኖረዋል። በወረዳው እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ተብለው የቀበሌ ቤት ለማግኘት ወረፋ እየጠበቁ ካሉ በርካታ ነዋሪዎች መካከል እንዷ ናቸው። ቤት ለማግኘት ተመዝግበው ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ቢሆንም "በወረዳው የቤት አሰጣጡ ሂደት ግልጽነትና ፍትሃዊነት የጎደለው በመሆኑ እስካሁን ባለቤት መሆን አልቻልኩም" ይላሉ። ቋሚ የገቢ ምንጭ እንደሌላቸውና በህመም የሚሰቃዩ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮዋ በአሁኑ ወቅት በኪራይ ለሚኖሩበት ቤት ክፍያ እንኳ የሚፈጽሙት በሰው እርዳታና ድጋፍ መሆኑን ያብራራሉ። "አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ የምኖርበት ቤት ባለንብረት ኪራይ የሚጨምሩ መሆኑን፤ መክፈል የማልችል ከሆነ ደግሞ እንደሚያስለቅቁኝ ተነግሮኛል፤ በዚህም የተነሳ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ልጄን ይዤ ጎዳና ልወድቅ እችላለሁ" ብለዋል። ወይዘሮ የሺ የቀበሌ ቤት ለማግኘት ለረጅም ዓመት ወረፋ እየጠበቁ ያሉ ቢሆንም ወረዳው ቅርብ ጊዜ ለገቡ የቤት ጠያቂዎች ቤት እየሰጠ መሆኑ አድሎዊ አሰራር አለ ይላሉ። እንጨት በመሸጥ የአልጋ ቁረኛ ልጃቸውን የሚያስታምሙት የእድሜ ባለፀጋዋ ወይዘሮ የሺ ኮዳኔም ተመሳሳይ አድል እንደገጠማቸው ነው የሚናገሩት። በኢኮኖሚ ገቢያቸው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በዚሁ ወረዳ የሚኖረት የማህበረሰብ ክፍሎች በየአካባቢያቸው የሚለቀቁ የቀበሌ ቤቶች የሚተላለፉት ከዚህ በፊት ላልተመዘገቡ እና ለወረዳው አስተዳዳሪዎች ቅርብ ለሆኑ ሰዎች ብቻ መሆኑን ይገልፃሉ። ወይዘሮ አዳነች አለሙ በበኩላቸው አባታቸው የሞቱባቸው ሶስት ልጆች የማሳደግ እዳ እንዳለባቸውናበቤት ክራይ በመንከራተት የሰው ልብስ በማጠብ የሰው አሻሮ በመቁላት እንደሚተዳደሩ ነው የተናሩት፡፡ ቀበሌ ቤት እንዲሰተኝ ከተየቅኩ ረጅም ጊዜ ቢሆነኝም ላገኝ አልቻልኩም ነው ያሉት፡፡ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 አስተዳደር ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ወረደሕሽ የእብዩ የቀበሌ ቤት አሰጣጥ ጉዳዩን በተመለከተ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ፤ በወረዳው በጠቅላላው 1 ሺህ 524 የቀበሌ ቤቶች ያሉ ሲሆን ቤት ፈላጊ ነኝ ብሎ የተመዘገበው ግን አንድ ሺህ ይጠጋል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ሁሉም የቀበሌ ቤቶች የተያዙ ቢሆንም በህገ-ወጥ መንገድ ቤቶቹን ይዘው ከሚገኙት በማስለቀቅ ተመዝግበው ከሚጠባበቁት መካከል በቤት እጦች በከፋ ችግር ውስጥ ያሉትን በመለየት ለመስጠት ጥረት አየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። የግል ቤት ሰርተው፣ የጋራ መኖሪያ ቤት አግኝተው ሳለ ይኖሩበት የነበረውን የቀበሌ ቤት ባላስረከቡ ላይ ባለፉት ሳምንታት በተደረገው አሰሳ 20 ያህል ቤቶችን ማግኘት ተችሏል። ያም ሆኖ ግን የእነዚህ ቤቶች ቁጥር ቤት እንዲሰጠው ከተመዘገበው ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ምክትል ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል። በመሆኑም እነዚህን ቤቶች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ለወደቁ፣ ረዳት ለሌላቸው አረጋዊያን፣ የአካል ጉዳተኞች ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። የቤት እደላውን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማከናወንም በራሱ በህዝቡ ምርጫ ኮሚቴ የተዋቀረ መሆኑን ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ አመራር መሰየሙን ተከትሎ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ መኖሪ ቤቶችን ለሚገባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የመስጠት ተግባር በስፋት አየተከናወነ ነው። ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች የቤት እደላው ከአድልኦ የፀዳና በትክክል ቅድሚያ ለሚገባቸው የከተማው ነዋሪዎች የሚደርሳቸው ስለመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። ከዘጠኝ ዓመት በፊት በወጣ መረጃ መሰረት በመላው አዲስ አበባ በተለምዶ "የቀበሌ ቤቶች" በሚል የሚታወቁት ቤቶች ቁጥር ከ173 ሺህ አይበልጥም። ከእነዚህ መካከል 85 በመቶዎቹ የመኖሪያ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ የንግድ ቤቶች ናቸው። አብዛኛዎቹ እነዚህ ቤቶች ቢሆንኑም እጅግ ያረጁና ለከተማ ነዋሪዎች እምብዛም ምቹ ያልሆኑ መሆናቸውም ይነገራል። የሆነው ሆኖ አራት ሚሊዮን ህዝብ ይኖርባታል በሚባልባት አዲስ አበባ ቤት ለማግኘት በተለያየ መንገድ ጥያቄ አቅርቦ እየተጠባበቀ ያለው ህዝብ ቁጥር በርካታ ነው። ችግሩ ሰፊ እና በከተማ ደረጃ ያለ በመሆኑ ለእነዚህ ዜጎች መፍትሄ ምን ሊሆን እንደሚችል የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲን ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት አልተሳካም።