ቀጥታ፡

በሀሰተኛ ማንነት የንግድ ሥራ የሚያከናውኑ 13 ድርጅቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ህዳር 14/2011 ኢትዮጵያ ውስጥ በሀሰተኛ ማንነት ደረሰኝ አሳትመው የንግድ ሥራ እንደሚያከናውኑ ከተደረሰባቸው ድርጅቶች መካከል 13ቱ መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። በሀሰተኛ ንግድ ፍቃድና ማንነት የሚንቀሳቀሱ 124 ድርጅቶች መኖራቸው በጥናት መረጋገጡን ሚኒስቴሩ በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል። እነዚህ ድርጅቶች ባለፉት ጥቂት ወራቶች ህጋዊ ከሆኑ ነጋዴዎች ጋር ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ ግብይት መፈፀማቸውም ተደርሶበታል። በዚህ ህገ ወጥ ግብይት አማካኝነት መንግስት ማግኘት የሚገባውን ከፍተኛ መጠን ያለው ገቢ ማጣቱም ተገልጿል። ሚኒስቴሩ ያለደረሰኝ ግብይት ማከናወን እንዲሁም ግብይት ሳይኖር ደሰረኝ መሸጥና መግዛት በሀገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። በሚኒስቴሩ የህግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ እንዳሉት፤ እውነተኛ ግብይት ሳያከናውኑ ደረሰኝ መሸጥም ሆነ መግዛት በታክስ አስተዳደር አዋጁ ወንጀል እንደሆነ ተቀምጧል። ተግባሩ የነጋዴዎች የሽያጭ መጠን እንዳይታወቅ በማድረግ መንግስት ትክክለኛ ግብር እንዳይወስን፤ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዳይኖር፣ የህዝቡ የልማት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዳያገኝ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ትልልቅ ድርጅቶች እየሰሩ ኪሳራ የሚያሳውቁበትና የተመላሽ የሚጠይቁበትን ምክንያት ለማወቅ በተካሄደው ጥናት መሰረት አንዱ በሀሰተኛ ማንነት ላይ የተመሰረተ ሀሰተኛ የደረሰኝ ግዥና ሽያጭ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል። በህገ-ወጥ ግብይት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በአገር ምጣኔ ኃብት ላይ የሚያደርሱት አሉታዊ ተፅዕኖ የጎላ በመሆኑ የቁጥጥርና ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል። በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሀሰተኛ ደረሰኝ ከሚንቀሳቀሱ 124 ድርጅቶች መካከል 13ቱን በደላሎች አማካኝነት እንዲያዙ ማድረጉን ነው ያስታውቀው በድርጅቶቹም ላይ ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ተናግራዋል። በሀሰተኛ ማንነት ላይ ተመስርተው ደረሰኝ የሚሸጡ 124 ድርጅቶች በአገሪቱ ያደረሱትን ምጣኔ ኃብታዊ ክስረት ለማወቅ ከእነዚህ ድርጅቶች ደረሰኝ የገዙ አካላት ላይ ኦዲት የሚካሄድ መሆኑንም አስታውቀዋል። ሸማቹ ደረሰኝ በመጠየቅ፣ ሚዲያው በማስተማር፣ የንግዱ ማኅበረተስ ህገ-ወጦችን በማጋለጥ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ትልልቅ ግብይት እያከናወኑ አነስተኛ ገቢ የሚያሳውቁ፣ ያለ ደረሰኝ ግብይት እያከናወኑ ተመላሽ የሚጠይቁ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በአገር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። "አንድ ነጋዴ ያለ ደረሰኝ በመሸጡ ለመንግስት ገቢ የሚሆነውን 15 በመቶ ለግል ጥቅሙ ከማዋሉም ባለፈ የግብር አወሳሰን ስርዓቱን ሚዛን የሚያዛባ ይሆናል" ብለዋል። በመሆኑም መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ የገለፁት አቶ ዘመዴ "ህገ-ወጦቹ ላይም የታክስ አስተዳደር አዋጁን መሰረት በማድረግ አስተዳደራዊ ርምጃ ይወስዳል፤ በወንጀልም ተጠያቂ ያደርጋል" ብለዋል። ባለፉት አስር ቀናት ብቻ በ18 ቦታዎች ላይ በተደረገ የቁጥጥርና የክትትል ስራ ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ 15 ድርጅቶች ለህግ ቀርበው ምርምራ እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል። በአገሪቱ የታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 መሰረት ያለ ደረሰኝ ግብይት ማከናወን እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት ያስከትላል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም