በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰትና የንግድ ግንኙነት በሚፈለገው መጠን አላደገም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰትና የንግድ ግንኙነት በሚፈለገው መጠን አላደገም ተባለ
አዲስ አበባ ህዳር 14/2011 በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰትና የንግድ ግንኙነት በሚፈለገው መጠን ለማሳደግ ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል ተባለ። ይህ የተባለው የኢትዮጵያና የቻይናዋ ዥንጃን ግዛት የኢንቨስትመንትና የንግድ ስምፖዚየም ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ሲከፈት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካዔል ባደረጉት ንግግር ነው። ሚኒስትር ዲኤታው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰትና የንግድ ግንኙነት እያደገ ቢሆንም እሚፈለገው መጠን ላይ አልደረሰም። ቻይና እና የአፍሪካ አገራት ባለፈው መስከረም በተካሄደው የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ላይ ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት በርካታ የቻይና ባለሃብቶች በተለያዩ የአፍሪካ አገራት መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሳስ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። የዚሁ እንቅስቃሴ አንድ አካል የሆነውና ከ70 ድርጅቶች የተወጣጡ መቶ ያህል ባለሃብቶችን ያካተተው የቻይና ልዑክ ላለፉት ሶስት ቀናት በኢትዮጵያ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት አድርጓል። በዛሬው እለትም ባለሃብቶቹ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የሚገናኙበትና በአገሪቱ ባለው የኢንቨስትመንት እድል ላይ የሚነጋገሩበት መድረክ ተዘጋጅቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አክሊሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት አገራቱ ወደ ቋሚ ድፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከገቡ 48 ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን በመካከላቸው ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትም እድገት እያሳየ ነው። በየአመቱ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት የንግድ ልውውጥ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል። እንዲያም ሆኖ አገራቱ ካላቸው የላቀ የትብብር ግንኙነት አኳያ አሁን ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የሚፈለግው ደረጃ ላይ አልደረሰም ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ለማድረግ የወሰደውን እርምጃና ቻይናም በትብብር ፎረሙ ላይ ያሳየችውን አቋም እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የንግድ ልውውጡን የበለጠ ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት ዶክተር አክሊሉ። የቻይናው የአለም አቀፍ ንግድ ትብብር ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበርና የንግድ ልኡካኑ መሪ ዥንግ ኩዋንግሻን በበኩላቸው ከኢትዮጵያም ሆነ ከአጠቅላይ አፍሪካ ጋር የሚያደርጉት የንግድ ትብብር የበለጠ የማሳደግ ተስፋ እንዳለ አንስተዋል። የልኡኩ መሪ በኮሙኒኬሽን፣ በመድሃኒት፣ በግብርና፣ በኢነርጂና ንግድ ላይ ትኩረት በማድረግ ከአቻ ተቋማት ጋር ምክክር እያደረጉ መሆኑንም አክለዋል። በመቀጠለም ንግግሩ ወደ ተጨባጭ ስራ እንዲሸጋገር የሚመለከታቸው ፖሊቲከኞች ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ትብበሩን ለማጠናከር ይቻል ዘንድም የቻይናው አለም አቀፍ ንግድ ትብብር ምክር ቤት የዥንጃን ግዛት ኮሚቴ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤቱን አዲስ አበባ ለመክፈት ዛሬ ስምምነት ተፈርሟል። በግዛቱ የሚገኘው የጤና ሳይንስ ኮሌጅም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።