የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ህዳር 14/2011 የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ለመሰረታዊ አገልግሎት ትራንስፎርሜሽን መርሃ ግብር 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ አደረገ። የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከባንኩ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ገብርኤል ንጋቱ ጋር ተፈራርመዋል። መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተተገበረ ሲሆን በጤናው ዘርፍ ፣ትምህርት፣የውሃና የንጽህና አገልግሎቶችን ጥራት ባለው መልኩ ተደራሽ ማድረግ ያካተተ ነው። የድጋፍ መርሃ ግብሩ በክልሎችና ወረዳዎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋልም ነው የተባለው። የባንኩ የምራስቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ገብርኤል ንጋቱ እንዳሉት፤ ባንኩ መንግሥት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ ባለው ጥረት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2006 ጀምሮ እየደገፈ ይገኛል። ለአብነትም በኃይል ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በውኃ አቅርቦት፣በንጽህና፣በግብርናና አስተዳደር ዘርፍ እየደገፈ መሆኑንም ጠቅሰዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የዛሬውን ስምምነት ጨምሮ ባንኩ እስካሁን የ1 ነጥብ 74 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ድጋፍ አድርጓል። ይህም ባንኩ ኢትዮጵያ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የምትሰራውን ስራ በቁርጠኝነት እንደሚደግፍም አመላካች ነው ያሉት። ባንኩ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ ገልጸው ድጋፉ በተለይ የሰው ኃብት ልማት ላይ የሚከናወነው ተግባር የተቃና እንደሚያደርግ ያላቸውን ተስፋም አክለዋል። በቀጣይም ባንኩ ከመንግስት ጋር በመተባበር የሚሰጠውን ድጋፋ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው መሰረታዊ አገልግሎቶችን በማቅረቡ በኩል ባለፉት ዓመታት አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል። ''ለዚህም የአፍሪካ ልማት ባንክ የሚመሰገን ድጋፍ አድርጓል'' ያሉት ሚኒስትሩ መሰረታዊ አገልግሎቶች በስኬት እንዲከናወን ቁልፍ ሚና መጫወቱን አብራረተዋል። መንግሥት የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል የሚሰጣቸውን መሰረታዊ አገልግሎቶች የበለጠ እንደሚያጠናክር የገለጹት አቶ አህመድ ዛሬ የተገኘው ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልም ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ሥራ ላይ ይውላል ብለዋል።