ቀጥታ፡

የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ላለፉት አራት ወራት ለተጫዋቾቹ ደሞዝ አልከፈለም ተባለ

አዲስ አበባ ህዳር 13/2011 በኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪሚየር ሊግ እየተካፈለ የሚገኘው ደደቢት እግር ኳስ ክለብ ከሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ለተጫዋቾቹ ደሞዝ  እንዳልከፈለ ተገለፀ። ቡድኑ ከፍተኛ የሆነ የበጀት ቀውስ እንደገጠመው ሥራ አስኪያጁ አቶ ሚካኤል ዓምደመስቀል ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ከትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት /ኤፈርት/ ይገኝ የነበረው የገንዘብ ድጋፍ ባለፈው ዓመት ቀንሶ እንደነበር፤ በዚህ ዓመት ደግሞ ሙሉ በሙሉ በጀቱ እንዳልተለቀቀ ነው ሥራ አስኪያጁ የገለፁት። በዚህም የተነሳ ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ክለቡ የሆቴል አገልግሎትን ጨምሮ ለ2011 ዓ.ም ጨዋታዎች የሚያስፈልገውን ዝግጅት እያከናወነ ያለው በእዳ ውስጥ ሆኖ እንደሆነ አስታውቀዋል። ከዚህም ሌላ በ2010 ዓ.ም በክለቡ የነበሩና አሁን የለቀቁ አንዳንድ ተጫዎችም ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ነው የተገለፀው። ከነዚህ ተጫዋቾች መካከል ለአብነት የተጠቀሰው ከደደቢት እግር ኳስ ክለብ በዚህ ዓመት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው ጌታነህ ከበደ  ነው። በበጀት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ደደቢት እግር ኳስ ክለብ በሶስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የፊታችን እሁድ ከደቡብ ፖሊስ ጋር እንደሚጫወት የመዋው መርሃ ገብር ያስረዳል። ይሁን እንጂ ክለቡ በገንዘብ ወጪ ምክንያት ጨዋታው እንዲራዘምለት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ መጠየቁን ሥራ አስኪያጁ አክለው ገልጸዋል። በ2011 የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ደደቢት እግር ኳስ ክለብ ባለበት የበጀት ችግር በሴቶች እንደማይሳተፍ ማስታወቁ ይታወሳል። የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ከዚህ በፊት መቀመጫው አዲስ አበባ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን ወደ ትግራይ ክልል መወሰዱም ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም