ባህርዳር የአዲስ አበባ እንግዶቿን ለመቀበል ተዘጋጅታለች - ኢዜአ አማርኛ
ባህርዳር የአዲስ አበባ እንግዶቿን ለመቀበል ተዘጋጅታለች
ባህር ዳር ህዳር 13/2011 በአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የሚመራውን የልኡካን ቡድን ለመቀበል መዘጋጀቱን የባህር ዳር ከተማ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስተወቁት በምክትል ከንቲባው የሚመራ ከ400 በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶችና የከተማው ነዋሪዎች ባህርዳርንና አካባቢውን ለመጎብኘት ነገ ባህር ዳር ይገባሉ። የልኡካን ቡድኑ ከህዳር 14 እስከ 16 ቀን 2011 ዓ.ም የሚያደርገው ቆይታም የተሳካ ለማድረግ የከተማው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። የልኡካን ቡድኑ ወደ ባህር ዳር መምጣት ከዚህ ቀደም የነበረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ አላማ ያለው መሆኑን ተናግረዋል። እንዲሁም በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በጋራ ተባብሮ በማስወገድ ለችግሩ በባለቤትነት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን በተግባር ለማሳየት ጭምር እንደሆነም አመልክተዋል። "የልኡካን ቡድኑ በቆይታውም ጭስ አባይ ፏፏቴን፣ የቤዛዊት ቤተመንግስትን፣ የባህር ዳር ብሄራዊ ስታድየምንና የጣና ገዳማትን እንዲጎበኙ ይደረጋል" ብለዋል። እንዲሁም በእንቦጭ አረም የተወረረውን የጣና ቂርቆስ ገዳም በመጎብኘት በቀጣይ በሚካሄደው አረሙን የማስወገድ ተግባር የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ግንዛቤ እንዲይዙ ይደረጋል። የባህርዳርና የአዲስ አበባ ከተሞች ከንቲባዎችም በቀጣይ እርስ በእርስ በሚደረግ ግንኙነትና የልምድ ልውውጥ በሚደረግበት ዙሪያም ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል። "ለልኡካን ቡድኑም ከነገ 11 ሰዓት ጀምሮ ከባህር ዳር ከተማ ወጣ ባለ ቦታ አቀባበል ለማድረግ ከአንድ ሺህ በላይ የከተማው ወጣቶችና ነዋሪዎች ዝግጅት አድርገዋል" ብለዋል። የኮሚቴው አባል አቶ ቃል ኪዳን ፀና በበኩላቸው ቀደም ሲል የነበረው ግንኙነት አንዳለ ሆኖ በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማረምና ለመተባበር የሚመጣውን የልኡካን ቡድን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል። ቡድኑን በምን አግባብ መቀበል እንደሚገባም በመወያየት የስራ ክፍፍል መደረጉን ጠቁመው፤ "ውንድማማችነትን በሚሳይ አግባብ ለመቀበል ተዘጋጅተናል" ብሏል። "የጣና ጉዳይ የባህር ዳር ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ብሎም የኢትዮጵያ ሃብት ነው ይህን ሃብት በባለቤትነት ለመጠበቅ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ያነሳሳል" ብለዋል። "ከተማችን ያለችበትን ሁኔታ ለማስጎብኘትና የከተማዋን ስምና ዝና ከፍ ለማድረግ የሚያግዝ ጉብኝት ለማድረግ ተዘጋጅተናል" ያሉት ደግሞ አቶ ተሾመ አበበ ናቸው። በተለይም የጣና ጉዳይ የእኛም ጉዳይ ነው ብለው መምጣታቸው ፍቅርንና ወንድማማችነትን ያጠነክራል" በማለት በቆይታቸው በጋራ በሚያገናኙ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።