ቀጥታ፡

በአእምሮ ጤና ላይ የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የኪነ ጥበብ ሚና ከፍተኛ ነው -ባለሙያዎች

አዲስ አበባ ህዳር 13/2011 በአእምሮ ጤና ላይ የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የኪነ ጥበብ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ። የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ስለራሳቸው መናገር የማይችሉ በመሆኑ ከኀብረተሰቡ እንዲገለሉ ተደርገዋል። ህሙማኑ ከገጠማቸው ችግር ለመታደግ የኪነ ጥበብ ስራዎች ሊበራከቱ እንደሚገባ ነው ባለሙያዎቹ የገለጹት። የፊልም ደራሲ፣ ዳይሬክተርና ፕሮዲዩሰር ዳንኤል በየነ የአእምሮ ጤና ችግር ገጥሟቸው ወንጀል በፈጸሙ ሰዎች ታሪክ ላይ ያጠነጠነ  "መንታ ነብስ" የተሰኘ ፊልም ሰርቶ ለእይታ አብቅቷል። በተጨማሪም በአዕምሮ ጤና ላይ ያተኮረ "የመሃን ምጥ" የተሰኘ ፊልም ለእይታ ያበቃ ሲሆን በአእምሮ ህመም ላይ የሚያጠነጥን ሦስተኛ ፊልም እየሰራ እንደሚገኝም ተናግሯል። "መንታ ነብስ" ፊልምን ሲሰራ የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በሚፈጽሙት ወንጀል ከጤነኛ እኩል እንደሚዳኙና ህመማቸው የሚታወቅላቸው ከተፈረደባቸው በኋላ መሆኑን እንደታዘበም ገልጿል። ''እኛ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በኩላሊት ህመም ላይ ያደረጉትን እገዛና መረዳዳት በማስታወስ ስለራሳቸው መናገርና ማስረዳት ለማይችሉት አእምሮ ህሙማንን መርዳት ይገባናል'' ብሏል። በኪነ ጥበብ ሥራዎች የኀብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የአእምሮ ህሙማን በሽታው ሳይጠናባቸው ወደ ህክምና ተቋም እንዲሄዱ የማድረግ ሥራ ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ አቅርቧል። የ"ኅረየት" ፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ብርሃኔ ጌታቸው በበኩሉ ፊልሙን ሲሰራ የህክምና ባለሙያ እርዳታ በመሻት ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ጎራ ባለ ጊዜ ያለውን ችግር ማየቱ በህመሙ ዙሪያ ለመስራት እንዳነሳሳው ተናግሯል። ለአራት አመታተ "ኅረየት" በሚል ርዕስ የተለያዩ የኪነጥበብ ስራዎችን የሰራው ብርሃኔ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ህመሙን ለመርዳት ትልቅ ሚና ቢኖራቸውም የሚጠበቅባቸውን ያህል አልተወጡም ብሏል። መንግስት ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ህሙማንን ለመርዳትና ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ተባብሮ መስራት እንዳለበት አብራርቷል። የኢትዮጵያ አዕምሮ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳዊት አሰፋ እንዳሉት በአእምሮ ጤና አገልግሎት ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ኪነጥበብ መፍቻ መንገድ ናት። የአእምሮ ጤና ህክምና ተደራሽነት አንዱ ችግር በመሆኑ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም