ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሳጅን ብርሃነ መስቀል ብዙነህ ላይ የስነ ምግባር እርምጃ ሊወስድ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 13/2011 የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሻምበል አራት አባል ሳጅን ብርሃነ መስቀል ብዙነህ ላይ የስነ ምግባር እርምጃ ሊወስድ ነው። በኮሚሽኑ የተወርዋሪ ኃይል ዲቪዚዮን የሻምበል አራት አባል ሳጅን ብርሃነ መስቀል እርምጃ የሚወሰደው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አርማ የሆነውን "V" ምልክት ዘቅዝቀው ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ጋር ፎቶ መነሳታቸውን ተከትሎ ማህበሩ ለኮሚሽኑ ባቀረበው ቅሬታ መሰረት ነው። ተግባሩ የስፖርት ማህበሩን "እጅጉን በማስቆጣቱ" የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አፈጣኝ እርምጃ እንዲወስድ በደብዳቤ ጠይቆ ነበር። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም የማህበሩን ጥያቄ ተመልክቶ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ምላሽ ሰጥቷል። የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ስፖርት ማህበሩ ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍትሕ አሰጣጥ ሂደቱ በሚያግዝ መልኩ መረጃውን አጠናቅሮ ማቅረቡን አመስግኗል። አንድ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅና ህግን ለማስከበር የተሰማራ የፖሊስ አባል መፈፀም የማይገባውን ተግባር የፈፀመ አባል በኮሚሽኑ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት በስራ ክፍሉ በኩል በከባድ ዲሲፕሊን ተከሶ ጉዳዩን መርምሮ እርምጃ እንዲወሰድበት ለኮሚሽኑ የከባድ ዲሲፕሊን አጣሪ ኮሚቴ የተላለፈ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም