ቀጥታ፡

የአየር መንገዱን እድገት ከአዲስ አበባ ጋር አጣጥመን በምንሄድበት መንገድ ላይ አብረን እንሰራለን-የከተማዋ ከንቲባ

አዲስ አበባ ህዳር 13/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ እድገት የከተማዋን ተጠቃሚነት እንዲያሳድግ አብረው እንደሚሰሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አስታወቁ። ምክትል ከንቲባው የአየር መንገዱን አጠቃላይ እንቅስቃሴና የተለያዩ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን የጎበኙ ሲሆን አየር መንገዱ ካሉበት በርካታ መንገደኞችና ደንበኞች አኳያ እየገጠመው ባለው የትራፊክ መጨናነቅ ዙሪያ ከአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ጋር ተወያይተዋል። ከተማዋ የበርካታ አየር መንገዶች በረራ መሸጋገሪያ እንደመሆኗ መጠን ከአየር መንገዱ ጋር አብሮ በመስራትና ለተጓዥቹ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ለከተማዋ ብሎም ለአገሪቷ በርካታ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት እንደሚቻልም ነው የተገለፀው። አየር መንገዱን በትክክል ከተጠቀምንበት "የሁላችንንም አቅም የሚያጎለብት ነው" ያሉት ምክትል ከንቲባው ከቦርዱ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩና አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ማስፋፊያውንም በተመለከተ ከከተማዋ እድገትና ከከተማዋ ነዋሪዎች ህይወት ጋር በሚጣጣም መልኩ ለማስኬድ አብረን እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል። የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ግበረማርያም በበኩላቸው አየር መንገዱ በዓመት 11 ሚሊዮን መንገደኞችን እንደሚያጓጉዝ ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ ግማሹን አገር ውስጥ ቆይታ እንዲኖራቸው ብናደርግ ከቱሪዝምና ከሌሎች ዘርፎች ብዙ ገቢ ማግኘት ይቻላል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ እንደ መሆኗ አየር መንገዱ ትልቅ ሚና እንዳለውና ይህን አቅም ለማስቀጠልም ሆቴልን ጨምሮ በርካታ ማስፋፊያዎች በመሰራት ላይ መናቸውን ገልጸዋል። ይህን ማስፋፊያ ከግብ ለማድረስም የከተማ አስተዳደሩ አብሮአችን መስራቱ በተለይ ቦታና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ትልቅ እድል አለው ሲሉም ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም