ቀጥታ፡

አፍላቶክሲን የቅመማ ቅመም ላኪዎች ጥቅምና የአገሪቱ ገቢ እንዲቀንስ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ ኅዳር 13/2011 አፍላቶክሲን ወደ ውጭ ከሚልኩት የቅመማ ቅመም ምርት የሚያገኙትን ጥቅምና አገሪቱ ከዘርፉ የምታስገባውን ገቢ እየቀነሰው መሆኑን የዘርፉ ባለሃብቶች አመለከቱ። በአፍላቶክሲን /ሻጋታ/ በከፍተኛ መጠን እየተጎዳ ያለውን የቅመማ ቅመም ዘርፍ ለመደገፍ ዘመናዊ የምርት አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋትና ህግ የማስከበር ተግባራት እንዲከናወኑም ጠይቀዋል። አገሪቱ ለቅመማ ቅመም ምርት ምቹ የአየር ንብረት ቢኖራትም የምግብ ደህንነትና ጥራት ችግሮች 'ተጠቃሚነቷን እያሳጧት ነው' ሲሉ ባለሃብቶቹ ለኢዜአ ተናግረዋል። አፍላቶክሲን አስፈርጊለስ ፍላገስና አስፈርጊለስ ፓራሲቲከስ በሚባሉ ሁለት አይነት የፈንገስ አይነቶች የሚመረት ጎጂ ንጥረ ነገር ነው። የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም አምራቾች፣ አቀነባባሪዎችና ላኪዎች ማህበር ስራ አስኪያጅና የኢትዮ-ሆላንድ የንግድ ትብብር ለግብርና ልማት የቅመማ ቅመም ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አዲሱ አለማየሁ "ዘርፉ በአፍላቶክሲን በከፍተኛ መጠን እየተጎዳ ነው" ይላሉ። ወደ ውጭ ከሚላከው የቅመማ ቅመም ምርት የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ መሆኑንም ገልጸዋል። በ2009 ዓ.ም ወደ ውጭ ከተላከ እርድ 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰው በ2010 ዓ.ም ከእርድ የተገኘው ገቢ ከ2 ሚሊዮን ዶላር አለመብለጡ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ገቢ እየተገኘ አለመሆኑን ለማሳያ አንስተዋል። ማህበሩ ከኢትዮ-ሆላንድ የንግድ ትብብር ለግብርና ልማት የቅመማ ቅመም ፕሮጀክት ጋር በመሆን ችግሩን የተመለከተ ጥናት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አስጠንቶ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክና ፎረሞችን በማካሄድ ማወያየቱን ገልጸዋል። ችግሮቹን በልምድ ልውውጥ ለመፍታት ወደውጭ አገራት በመሄድ በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎችን የሚያሳትፉ መድረኮችም አካሂዷል። የአፍላቶክሲን መጠን ናሙናዎችን በላቦራቶሪ በማሰራት በተገኘ ውጤት ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ላኪዎች ጋር እስኪደርስ እየጨመረ መምጣቱን መለየቱንም አቶ አዲሱ አስረድተዋል። አፍላቶክሲን በምርት አሰባሰብና አያያዝ ችግር የሚከሰት መሆኑን ጠቁመው መፍትሄ ያሏቸውን ዘረዝረዋል። የሻጋታ ተጋላጭነት የሚጨምሩ እርጥበትና ሙቀትን ለመከላከል የምርት አሰባሰብና ክምችት ስራ በቴክኖሎጂ መደገፍ አለበትም ብለዋል። ትርፍ ለማግኘት ሲባል ምርትን ከባዕድ ነገር ጋር የሚቀላቅሉ በመኖራቸው እነዚህንም በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። የማህበሩ የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ሚሊዮን ቦጋለ በበኩላቸው ተመሳሳይ ጥራት ያለውን የኢትዮጵያና የህንድ እርድ ለአብነት አንስተው የኢትዮጵያው በምርት አሰባሰብ ሂደት ጥራቱን እንደሚያጣ ተናግረዋል። ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባ በመጠቆም። "በቅመማ ቅመም ዘርፍ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የጥራት ችግር መኖሩን ለይተናል" ያሉት ደግሞ የቡናና ሻይ ባለስልጣን የልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አውግቸው ተሾመ ናቸው። በርበሬ ኪሎ እንዲጨምር ውሃ ማርከፍከፍ፣ እርድንም አስመስሎ የመስራት ተግባር እየተስተዋለ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ስልጠናና ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራት እየተከናወኑ ነው፤ የአርሶ አደሩ የምርት አሰባሰብና አያያዝ ለማሻሻልም ስልጠና እየተሰጠ ነው። ዘርፉን በቴክኖሎጂና በህግና ስርዓት ለመምራት የግብይት ስርዓት አዋጅ ተዘጋጅቶ የተለያዩ አካላት እየተወያዩበት መሆኑን ገልጸዋል። ችግሮቹ ተወግደው አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የህግ ማዕቀፉ መጠናቀቅ ወሳኝ እንደሆነም አክለዋል። በአፍላቶክሲን ምክንያት ወደ እንግሊዝና ጀርመን የተላከ በርበሬ መመለሱና አገሪቱም ከዘርፉ ታገኝ የነበረውን ገቢ ማጣቷ ይታወሳል። ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም የቅመማ ቅመም ምርቶችን ወደ ወጪ በመላክ 15 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ያገኘች ሲሆን በ2010 ዓ.ም ያገኘችው ገቢ ወደ 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር መውረዱን ከቡናና ሻይ ባለስልጣን የተገኘ መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም