ቀጥታ፡

ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አራቱ ለሌላ ጊዜ ተላልፈዋል

አዲስ አበባ ህዳር 13/2011 ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አራቱ በአህጉራዊ የክለብ ውድድሮችና ሌሎች ምክንያቶች ለሌላ ጊዜ መተላለፋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። የ2011 ዓ.ም የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከጥቅምት 25 ቅን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅትና ሌሎች ምክንያቶች ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል። የሊጉ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብሮች ከነገ ጀምሮ መካሄድ ይጀምራሉ። ህዳር 15 ቀን 2011 ዓ.ም መከላከያ ከድሬዳዋ ከተማ፣ ህዳር 16 ቀን 2011 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባ ጅፋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በቅደም ተከተል መከላከያና ጅማ አባ ጅፋር በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫና በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ባለባቸው ጨዋታ ሳቢያ ተራዝሟል። በተጨማሪም ህዳር 15 ቀን 2011 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ህዳር 16 ቀን 2011 ዓ.ም መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከፋሲል ከተማ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የፕሮግራም ማስተካከያ በማስፈለጉ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የሊግ ኮሚቴ አስታውቋል። የተራዘሙት መርሃ ግብሮች በተስተካካይ ጨዋታዎች እንደሚያዙና ጨዋታዎቹ የሚካሄዱበት ጊዜ ይፋ እንደሚሆን ፌዴሬሽኑ ገልጿል። ቀሪዎቹ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብሮች በተያዘላቸው ጊዜ ይከናወናሉ። በዚሁ መሰረት ነገ በሃዋሳ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ሲዳማ ቡና ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀለው ባህርዳር ከተማ ጋር ይጫወታል። ከነገ በስቲያ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ደቡብ ፖሊስ ከደደቢት በሃዋሳ ስታዲየም ይጫወታሉ። እሁድ ህዳር 16 ቀን 2011 ዓ.ም በሽሬ ስታዲየም ስሑል ሽረ ከአዳማ ከተማ፣ በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። በሌላ በኩል በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅቶችና ሌሎች ምክንያቶች ያልተካሄዱ ቀሪ የሁለተኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ወደፊት በሚገለጹ ቀናት እንደሚከናወኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች መቐለ ሰብአ እንደርታና ኢትዮጵያ ቡና ስድስት ነጥብ በመያዝ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋር በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አዳማ ከተማ፣ ደደቢትና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም