ቀጥታ፡

ባንኩ ለሴቶች ሥራ ፈጠራ ልማት መርሃ ግብር የ30 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ፈቀደ

አዲስ አበባ ህዳር 13/2011 የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ ለሴቶች ሥራ ፈጠራ ልማት መርሃ ግብር የ30 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ፈቀደ። የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከባንኩ ፕሬዘዳንት ወርነር ሆየር ጋር ዛሬ የብድር ስምምነቱን ተፈራርመዋል። ብድሩ በሴቶች የሚመሩ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችና የሥራ ፈጠራ መርሃ ግብሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የተገለጸው። ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የብድር፣ የአምራቹ ዘርፍ የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠና እንዲሁም ሙያዊ ክህሎትን የሚያሻሻሉ ስልጠናዎች እንዲያገኙ ማድረግ ሌላው የብዱሩ ዓላማ መሆኑ ነው የተመለከተው። ከዚህ በተጨማሪም በገጠርና ከተማ በጥቃቅና አነስተኛ የተደራጁ ሴቶች ብድር እንዲያገኙ በማስቻልም የሚገጥማቸውን የፋይናንስ ችግር ያቃልላል። ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እንደተናገሩት፤ መንግሥት ሴቶች በኢኮኖሚው ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የተለያየ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ከነዚሁ ተግባራት መካከል ተደራጅተው በኢኮኖሚው መስክ እንዲሰሩ ማድረግ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የፋይናስ አቅርቦት ችግር ግን ትልቅ ማነቆ ሆኖ መቀየቱን ገልጸዋል። የአውሮፓ ኢቨስትመንት ባንክ የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የሆነውን የሴቶች ተጠቃሚነት በመደገፉም ምስጋና አቅርበው ብድሩ የፋይናንስ እጥረቱን በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። የሴቶች ሥራ ፈጠራ ልማት መርሃ ግብር ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን በ 2013 መጀመሩን አስታውሰው፤ መርሃ ግብሩ በከተማና ገጠር በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ሴቶች ገቢ እንዲያድግ ማድረጉንም ተናግረዋል። በመርሃ ግብሩ 4 ሺህ 500 ሴቶች ብድር ማግኘታቸውን የጠቆሙት አቶ አህመድ ''ዛሬ የተፈራርመነው የብድር ስምምነት የሴቶች የፋይናንስ ተደራሽነትን እንደሚያሳድገው አስረድተዋል። ከዚህ ባለፈም ብድሩ በመርሃ ግብሩ አዳዲስ ለሚካተቱ ሴቶች የብድር እጥረት እንዳይገጥም አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚኖረው አስተዋጽኦም የጎላ መሆኑን አብራርተዋል። የባንኩ ፕሬዝዳነት ወርነር ሆየር በበኩላቸው ሴቶችን ማብቃት የቢዝነስ ውጤታማነትንና እድገትን ለማስፋፋትና ማህበራዊ  ፍትህን ለማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። ''ባንኩ የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶች አቅም እንዲጎለብት የሚያደርገውን ጥረት ይደግፋል'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የዛሬ ብድሩም የድጋፉ አካል መሆኑን አመልክተዋል። በቅርቡ መንግሥት በካቢኔ መዋቅር ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሴቶች እንዲሆኑ ማድረጉ ለጾታ እኩልነት ቁርጠኛ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸው በኢኮኖሚው መስክ የሚደረገውን ጥረትም ባንኩ እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም