በመቀሌ ከተማ ዘመናዊ ሕንጻዎችና የእግረኛ መንገዶች አካል ጉዳተኞችን ግምት ውስጥ ያስገቡ እንዳልሆነ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በመቀሌ ከተማ ዘመናዊ ሕንጻዎችና የእግረኛ መንገዶች አካል ጉዳተኞችን ግምት ውስጥ ያስገቡ እንዳልሆነ ተጠቆመ
መቀሌ ህዳር 13/2011 በመቀሌ ከተማ የሚገነቡ ዘመናዊ ሕንጻዎችና የእግረኛ መንገዶች የአካል ጉዳተኞችን ችግር ግምት ውስጥ ያስገቡ ባለመሆናቸው በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ እንቅፋት እየፈጠረባቸው መሆኑን አካል ጉዳተኞች ተናገሩ። የችግሩ ዋንኛ ምክንያት ተጠያቂነት ያለበት የዲዛይንና የግንባታ ስርዓት ተግባራዊ ሳይደረግ በመቆየቱ መሆኑን የመቀሌ ከተማ ህንጻ ሹም ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበር አባል የሆኑት ወይዘሮ ዘነበሽ ጌታነህ ለኢዜአ እንደገለጹት በመቀሌ ከተማ ተዘዋውረው የተመለከቷቸው ዘመናዊ ሆቴሎች የዊልቸር መግቢያና መውጫ በር የላቸውም፡፡ በስብሰባም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሆቴሎች በሚመጡበት ወቅት የሥራ ባልደረባዎቻቸውና ጓደኞቻቸው በሆቴሉ መዘዋወር ሲችሉ እሳቸው ግን ከመሰብሰቢያ አደራሹ ሳይወጡ ለመቆየት እንደሚገደዱ ተናግረዋል። ዘመናዊ ሆቴሎችም ሆኑ የተለያዩ ሆቴሎች አካል ጉዳተኞችን ከግምት ውስጥ ያስገቡ ባለመሆናቸው ከመጸዳጃ ቤት ጀምሮ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ አካል ጉዳተኞችን አስመልክተው የወጡ ህጎችና ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ አመራር አለመኖር የችግሩ ዋንኛ መንስኤ እንደሆነም ወይዘሮ ዘነበሽ ተናግረዋል፡፡ ከዓይነ ስውራን የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ገብረኪዳን ሐዱሽ እንደገለጹት ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮን ጨምሮ 14 ቢሮዎች የሚገለገሉበት ባለስድስት ወለል ህንጻ የዊልቸውር መግቢያ በር የላቸውም፡፡ አቶ ገብረኪዳን እንዳሉት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች የአካል ጉዳተኞችን ችግር በመስማትና በማየት መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት የላቸውም፡፡ "አካል ጉዳተኞች በየየሄድንበት ተቋም ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላችን እየተቸገርን ነው" ያሉት አቶ ገብረኪዳን ይህም ከህብረሰቡ ለመገለልና ለማህበራዊ ግንኙነት ችግሮች እየዳረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የትግራይ አካል ጉዳተኞች ፎረም ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ገነት ግርማይ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራ አካል ባለመኖሩ እየተቸገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የመቀሌ ህንጻ ሹም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክንፈ ግርማይ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት መልስ በአካል ጉዳተኞች የተነሳው ችግር ትክክለኛ መሆኑን አምነዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች የተሰጡ መብቶችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ምክር ተሰጥቷቸው ያለፈጸሙ 18 ግንባታዎች የማስጠንቀቂያና የገንዘብ ቅጣት እንደተወሰነባቸውም ገልጸዋል። እንደኃላፊው ገለጻ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቀናጀ ሥራ ተጀምሯል። አካል ጉዳተኞችን ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ህንጻዎችና መንገዶች እንዳይሰሩ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት። በትግራይ ክልል ከ89 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት ከትግራይ አካል ጉዳተኞች ፎረም የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡