ቀጥታ፡

ቤተክርስትያኗ ተቋርጦ የቆየውን የሙዝየም ግንባታ አስጀመረች

አክሱም ግንቦት 16/2010 በአክሱም ከተማ ለሶስት አመት ተቋርጦ የቆየው የሙዝየም ግንባታ መጀመሩን የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍጹም ብርሃን ለኢዜአ እንደገለጹት የሙዝየሙን ግንባታ እያካሄደች ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወሀዶ ቤተክርስትያን ናት። "ቤተክርስትያኗ የተቋረጠውን ግንባታ ለማስቀጠል 160 ሚሊዮን ብር በጀት ብትመድብም በቂ ባለመሆኑ ቀሪውን ገንዘብ  ከህዝብና ከባለሀብቶች ለማሰባሳብ በሚደረገው ጥረት ፅህፈት ቤቱ ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል ። የሙዝየሙ መገንባ በሁለት አመት ውስጥ ሲጠናቀቅ በቤተክሪስተያኑ  ውስጥ ተከማችተው ለአደጋ የተጋለጡ በርካታ ቅርሶች  ለእይታ የሚቀርቡበት አመቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ሀላፊው አመላክተዋል ። "ሙዝየሙ የአከባቢውን ባህላዊና ታሪካዊ እሴት ጠበቆ እየተገነባ ነው " ያሉት ሀላፊው ለቱሪዝም ልማትና ለምርምር ስራዎች የላቀ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስታውቀዋል ። የአክሱም ጽዮን ማሪያም ርእሰ ገዳማት ወአድባራት ምክትል ሰበካ ጉባኤ ሊቀ ካህናት አባ ተክለሃይማኖት አሳየሀኝ በበኩላቸው ቤተክርስትያኗ ባጋጠማት የበጀት እጥረት የሙዝየሙ ግንባታ ተቅርጦ መቆየቱን ተናግረዋል ። ሙዝየም ባለመኖሩ ዘመናት ያስቆጠሩ ቅርሶች  በቦታ ጥበት ለብልሽት መዳረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ "ጥንታዊ የብራና መጽሐፍት፣ የነገስታት አልባሳት፣ ጥንታዊ ስእሎችና መስቀል ባልተመቻቸ ቦታ ከመቀመጣቸው ባለፈ ለመጎብኘት እድል ሳያገኙ ቆይተዋል" ብለዋል ። "የሙዝየሙ  መገንባት  ቅርሶች በተመቻቸ ቦታ ተቀምጠው ለትውልድ እንዲተላለፉና ለቱሪስቶች እይታ እንዲበቁ ይረዳል" ሲሉ ተናግረዋል ። በ2ሺህ 140 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈው የሙዝየሙ ግንባታ ስራው 50 በመቶ ደረጃ ላይ እደደረሰ  ታውቋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም