ቀጥታ፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የ123 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ አጸደቀ

አዲስ አበባ ህዳር 13/2011 የአፍሪካ ልማት ባንክ የ123 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እርዳታ ለኢትዮጵያ አጸደቀ፡፡ ገንዘቡ ለያዝነውና ለሚቀጥለው ዓመት ለአገራችን መሰረታዊ የአገልግሎት ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም እንደሚውል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ድጋፉ የሁለተኛውን የኢትዮጵያ መንግስት እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል የሆነውን የሰው ሃብት ልማትና የቴክኖሎጅ አቅም ግንባታን ለማፋጠንና ዘላቂ ለማድረግ ያግዛል ተብሏል። ተቋሙ፣ ድጋፉን የሚያደርገው ኢትዮጵያ በሰው ሃብት ልማት ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቷን በተለይም የህጻናት ሞትን መቀነሷንና የገጠር ውሃ አቅርቦት ከፍ ማድረግ መቻሏን በምሳሌነት አንስቷል፡፡ የመሰረታዊ አገልግሎት ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም፣ የአፍሪካ ልማት ፈንድና የኢትዮጵያ መንግስት ዓለም ባንክን ከመሰሉ የልማት አጋሮች ጋር በቅንጅት ያዘጋጁት መሆኑ ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያን አበረታች ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብና አመርቂ የመዋቅር ሽግግር በማድረግ ላይ የምትገኝ ሃገር በሚል ዝርዝር አካቷታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም