የኦሮሚያ ልማት ማህበር ጂቡቲ ከሚገኙ የማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች ጋር ውይይት አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ልማት ማህበር ጂቡቲ ከሚገኙ የማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች ጋር ውይይት አደረገ
አዲስ አበባ ህዳር 12/2011 የኦሮሚያ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ኢቲቻ በጂቡቲ ከሚኖሩ የማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች ጋር ውይይት አደረጉ። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሻምቦ ፊታሞ በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የለውጥ መንፈስና መነቃቃት በመጠቀም ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሰላም፣ ዕድገትና ልማት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሚረባረቡበት ወቅት መሆኑን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጸህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። አምባሳደሩ ዳያስፓራው የሚገጥሙትን ችግሮችን በተደራጀ መልኩ በመለየትና የመረጃ ዕጥረትን በመቅረፍ ከኤምባሲው ጋር በይበልጥ ተቀራርቦ መስራት የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ ኤምባሲው በጅቡቲ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ መብትና ጥቅም ለማስከበር ከጅቡቲ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ተናግረው ሁሉም ለአገሩ በአንድነት መንፈስ መቆም እንዳለበት ከአደራ ጋር አሳስበዋል። አቶ ደጀኔ ኢቲች በበኩላቸው የማህበሩን አመሰራረት፣ ማህበሩ በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች እና ስኬቶች እንዲሁም ማህበሩ በቀጣይ የነደፋቸውን የልማት ፕሮጀክቶች በተመለከተ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡ አቶ ደጀኔ ማህበሩ 25ኛ ዓመቱን በሚያከብርበት በዚህ ልዩ አገራዊ የለውጥ የዕርቅና የንቅናቄ ወቅት አባላቱን ለማብዛትና ቅርንጫፎቹን ለማጠናከር በሰፊው እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝና የጅቡቲ ጉዞውም የዚህ አካል መሆኑን መግለጻቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።