አረጋውያን ለሕዝቦች አብሮነትና ሰላም መጎልበት ያላቸውን መልካም ተሞክሮ ለትውልድ እንዲያስተላልፉ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
አረጋውያን ለሕዝቦች አብሮነትና ሰላም መጎልበት ያላቸውን መልካም ተሞክሮ ለትውልድ እንዲያስተላልፉ ተጠየቀ
ሰመራ ህዳር 12/2011 አረጋውያን ለሕዝቦች አብሮነትና ሰላም መጎልበት ያላቸውን መልካም ተሞክሮ ለትውልድ በማስተላለፍ ሚናቸውን እንዲወጡ የአፋር ክልል ሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጠየቀ ። ቢሮው ”ቀደምት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን በመዘከር የኢትዮጵያ አረጋውያንን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እናረጋግጥ!” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን በጭፍራ ወረዳ አክብሯል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ያሲን እንዳስገነዘቡት አረጋውያን መልካም ኢትዮጵያዊ እሴቶች በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥሉ ተሞክሯቸውን ለአዲሱ ትውልድ ማካፈል ይጠበቅባቸዋል። አረጋውያን ትናንት ለሰላም፣ ለልማት እንዲሁም ለሕዝቦች አብሮነት የተጫወቱትን ሚና ዛሬም ለአገራዊ የሰላም እሴት ግንባታና የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር አገራዊ ኃላፊነታቸውንም ለመወጣትና ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጠይቀዋል። የክልሉ መንግሥት ተደራጅተው መብታቸውን ለማስከበርና ችግሮቻቸውን ለመፍታት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውም ገልጸዋል። በበዓሉ ከተሳተፉት አረጋውያን መካከል አቶ ሞሚን አስበራ በወረዳቸው የአረጋውያን ማህበር በማቋቋም የጤናና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉና ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በተጨማሪም ለወጣቱ ሕይወት ተሞክሯቸውን በማካፈል አገሩን ወዳድ ዜጋ እንዲሆን ኃላፊነቴን እወጣለሁ ብለዋል። ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ አቶ ኢሴ ኡርቶ ''መንግሥት ባመቻቸልን ዕድል ተጠቅመን በማህበር ተደራጅተን በማንቀሳቀስ ያለንን ልምድ ለትውልድ የምናስተላልፍበትና እንዲሁም የተሻለ ተጠቃሚም የምንሆንበት ሁኔታ መፍጠር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በአፋር ክልል በ11 ወረዳዎች የአረጋውያን ማህበራት ቢኖሩም፣ በአባላቱ ልምድ ማነስና ድክመት እንዲሁም በመንግሥት ትኩረት ማነስ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት ከአምስት እንደማይበልጡ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል። ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን ዘንድሮ የተከበረው በኢትዮጵያ ለ27ኛ፣በክልሉ ደግሞ ለሰባተኛ ጊዜ ነው።