በሰሜን ሸዋ ዞን ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና በዘመቻ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና በዘመቻ እየተካሄደ ነው
ደብረብርሃን ህዳር 11/2011 በሰሜን ሸዋ ከ14 ሺህ በላይ ለሚበልጡ ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና በዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን የዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ። ህክምናው እየተሰጠ ያለው የዓይን በሽታ ችግር እንዳለባቸው በጥናት ለተለዩ ሰዎች ነው፡፡ በካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ ለአንድ ወር ያህል በሚሰጠው የነጻ ህክምናው 41 ባለሙያዎች ሰልጥነው መሰማራታቸውን በመምሪያው የዓይነስውርነት መከላከል ኦፊሰር ወይዘሮ አበባ ነጋሽ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በተሰጠው የነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና 530 ሰዎች ተጠቃሚ ማደረግ እንደተቻለ አመልክተዋል። ሞጃና ወደራ፣ ሀገረማሪያም፣ ሲያደብርና ዋዩ፣ አንጾኪያ ገምዛ፣ ኤፍራታ ግድም፣ እንሳሮ፣ ቀወትና ጣርማ በር ወረዳዎች ህክምናው የሚሰጥባው ናቸው፡፡ የሚሰጠውን ነጻ የዓይን ህክምና ማህበረሰቡ በመጠቀም ከበሸታው ተፈውሶ ዓይነ ስውርነትን መከላከል እንደሚነርበትም ኦፊሰሯ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ሰሜን ሸዋ ዞን የትራኮማ ማጥፋት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ መሃመድሳኒ ሀሰን በበኩላቸው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ለሚያፈልጋቸው 14 ሺህ ሰዎች የሚሆን 15 ሚሊዮን 300ሺህ ብር በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተጓዳኝም ጥናት በማድረግ ተጨማሪ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንደሚሰጥ አመልክተው በትራኮማና በዓይነ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ጉድለት ሳቢያ የዜጎችን ዓይን ከጉዳት ለመታደግ በትኩረት እንደሚሰሩም አስረድተዋል፡፡ በሞጃና ወደራ ወረዳ የዙብአምባ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገደለ ማሞ በተደረገላቸዉ ቀዶ ህክምና የዓይን ብርሃናቸውን መልሰው እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ በተደረገላቸው ህክምናም ቀደም ሲል በዓይን ህመም ይሳቃዩ የነበረው አሁን መዳናቸውንና ያለችገር ማየት እንደቻሉ ገልጸዋል። " ባለፈው ዓመትም አንድ ዓይኔን ታክሜ ለውጥ በማየቴ ሌሎችንም በማስተባበር እንዲታከሙ ለማድረግ የደርሻዬን እወጣለሁ "ብለዋል፡፡ ሌላዋ የፊላገነት ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ንጋት አደናግር በበኩላቸው የዓይናቸው ጸጉር በመቀልበሱ ማየት ሳይችሉና ለመስራትም ይቸገሩ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ በግላቸው ለመታከምም የገንዘብ ችግር እንደነበረባቸው ጠቅሰው አሁን በነፃ በተሰጣቸው ህክምና የዓይን ብርሃናቸውን መልሰው ማግኘታቸው መደሰታቸውን አስረድተዋል። በዞኑ ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከ29 ሺህ በላይ ሰዎች የበሽታው ተጠቂ እንደነበሩም ተመልክቷል፡፡