ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአፍሪካ ህብረት በተለያየ የኃላፊነት ቦታ ላይ ከሚገኙ ሴት ኮሚሽነሮች ጋር ተወያዩ

88
አዲስ አበባ ህዳር 10/2011 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአፍሪካ ህብረት በተለያየ የኃላፊነት ቦታ ላይ ከሚገኙ ሴት ኮሚሽነሮች ጋር ዛሬ ተወያዩ። ፕሬዚዳንቷ በአፍሪካ ህብረት በተለያየ የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ብዛታቸው ከ30 የሚበልጥ ሴት ኮሚሽነሮችና አመራሮችን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በአፍሪካ ሴቶች በመሪነት እና በማህበረሰብ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው ውይይቱ ያተኮረው። በአፍሪካ የሴቶችን የመሪነትና በማህበረሰቡ ያላቸውን ሚና ማሳደግ እስካልተቻለ ድረስ የአህጉሪቱን ህዳሴ ማረጋገጥ እንደማይቻል በውይይቱ ላይ ተገልጿል። በመሆኑም በተለያዩ የአመራር ቦታዎች ላይ የሚገኙ አፍሪካዊያን ሴቶች ይህንን ለመቀየር በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም ተጠቅሷል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የቀድሞ ሊቀመንበር ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር ሆነው መሾማቸው እንደ አፍሪካዊ ሴት የሚያስደስትና የሚያኮራ ነው። በአፍሪካ ህብረት የገጠር ግብርና እና ኢኮኖሚ ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሊዮናል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በርዕሰ ብሄርነት መምረጣቸው ለአፍሪካ እንደ አርዓያ ሊወሰድ የሚችል ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም