ቀጥታ፡

ለገሃር አካባቢ በሚገነባው የተቀናጀ የመኖሪያና አገልግሎት መስጫ ፕሮጀክት ውስጥ መንግስት 27 በመቶ ድርሻ ኃብት ይኖረዋል ተባለ

አዲስ አበባ  ህዳር 10/2011 በአዲስ አበባ ለገሃር አካባቢ በሚገነባው የተቀናጀ የመኖሪያና አገልግሎት መስጫ ልማት ፕሮጀክት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት 27 በመቶ ድርሻ ኃብት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያስታወቁት ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ዛሬ በተከናወነው ስነ-ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። በዚሁ ንግግራቸው 50 ቢሊዮን ብር የሚወጣበት ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች ሳያፈናቅል፤ ተጠቃሚነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ ነው የሚገነባው በማለት አረጋግጠዋል። "መንግስት በፕሮጀክቱ ውስጥ 27 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው የተደረገው "ባለሃብቶች ለልማት ቦታውን ወስደው ለዓመታት ከማቆየት ባሻገር ካለሙ በኋላም ትክክለኛ ገቢያቸው ስለማይታወቅ ከተማው የሚገባውን ገቢ አያገኝም፤ በመሆኑም ባለድርሻ በመሆን እያንዳንዱን ገቢና ወጪ ማወቅ ስለሚቻል ለመቆጣጠርም ይረዳል" ብለዋል። ፕሮጀክቱ በሚገነባበት ወቅትም በአካባቢው የሚኖሩ 1 ሺህ 600 ያክል ዜጎች አካባቢያቸውን የማይለቁ ሲሆን ከባለሃብቶቹ በተገኘ  ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብርም የተሻለ መኖሪያ ቤት እንደሚገነባላቸው አስረድተዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታም የለገሃር አካባቢን ታሪካዊ ይዘት ሳይለቅ እንደሚካሄድ የገለፁት ዶክተር ዓብይ፤ በቀጣይም መሰል የመንደሮች ግንባታ እንደሚካሄድ ነው የተናገሩት። በአዲሱ መንደር በአጠቃላይ ከ4 ሺህ በላይ የመኖሪያ አፓርታማዎች ይገነባሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም የከተማዋን የቤት እጥረት ለማቃለል ይረዳል ብለዋል። ዛሬ በይፋ የተጀመረው ፕሮጀክት አጠቃላይ ግንባታ ከ5 እስከ 7 አመት የሚፈጅ ሲሆን፥ የመንደሩ የመጀመሪያ ሞል ግንባታም በሶስት አመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። መቀመጫውን አቡ ዳቢ ባደረገው ኤግል ሄልስ ኩባንያ የሚገነባው ይህ መንደር 36 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን 50 ቢሊየን ብር ወጪ ሲደረግበት፥ ለ25 ሺህ ሰው የስራ እድል ይፈጥራል ነው የተባለው። በውስጡም ሶስት ዘመናዊ ባለ 4 እና 5 ኮኮብ ሆቴሎችን፣ የመኖሪያ አፓርታማ፣ የንግድ እና የመዝናኛ ስፍራ እንዲሁም ግዙፍና ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ይኖረዋል። ''የኤግል ሂልስ'' ሊቀ መንበር ሙሃመድ ኣላበር በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር "መንግስት ሀገርና ህዝብ በሰጡት ትልቅ ቦታ የተነሳ ጉዳዩ የህንጻ ማቆም ብቻ ሳይሆን ሃገርና ህዝብ የሚቀይር ስራ እንዲሆን በመፈለጋቸው መሆኑን ተከትሎ ፍላጎታችሁን ለማሟላት እንሰራለን" ብለዋል። በመጨረሻም በተለይም ወጣቱ ለፕሮጀክቱ ስኬት በባለቤትነት መንፈስ እንዲንቀሳቀስም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም